የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ፡ ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት 6ኛ አጠቃላይ የፋይናንስ ጉባኤ በስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባኤው ላይ ከ300 በላይ በፋይናንስ ሴክተር ሙያ ውስጥ ያሉ የዘርፉ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አማካሪዎች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ የአለም አቀፍ ኩባንያዎች ተወካዮች፣ የኢኮኖሚ ተንታኞችና ተመራማሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም በዘርፉ አንቱ የተባሉ በምስራቅ አፍሪካና በሌሎችም ሀገራት የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፈዋል።
ለፖሊሲ አውጪዎችና አጥኚዎች መላ የሚያቀብሉ የጥናት ወረቀቶችም ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአይ_ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ እንደገለጹት ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው በዚሁ ጉባኤ የፋይናንስ አካታችነት፣ የአፍሪካ ቀጠና ኢኮኖሚ ጉዞና የኢትዮጵያ አሁናዊ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት፣ የካፒታል ገበያ፣ የዲጅታል ፋይናንስ ጉዞ እንዲሁም የፋይናንስ ሊበራላይዜሽን ዙሪያ ያለው አጠቃላይ የፖሊሲ ውሳኔና ተግባራቸው ይፈተሻል።
ከዚህ በፊት የተካሄዱ አምስቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ፋይናንስ ጉባኤዎች አዳዲስ ሀሳቦችን ወደፊት አምጥቷል ብለዋል።
ይኸኛው ጉባኤ ከምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ አቅጣጫዎች በተጨማሪ በዓለም አቀፍና ቀጠናዊ የፋይናንስ ችግሮች ዙሪያ በመምከር የቀጣይ መፍትሄ አማራጮችን ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል።
ጉባኤውን ያዘጋጁት አይ_ካፒታል አፍሪካ ኢንስትቲዩት፣ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና ከሌሎችም ጋር በመተባበር ነው።
ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ