የጂንካ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች ከሰብአዊ መብት አያያዝ አኳያ እያደረገ ያለው ተግባር ጠንካራ ነው – የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት

የጂንካ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች ከሰብአዊ መብት አያያዝ አኳያ እያደረገ ያለው ተግባር ጠንካራ ነው – የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት

ሀዋሳ፡ ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ማረሚያ ተቋም ታራሚዎች ከሰብአዊ መብት አያያዝ አኳያ እያደረገ ያለው ተግባር በጥንካሬ በደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ተገመገመ።

ማረሚያ ተቋሙ በቅጥር ግቢው ከመዋዕለ-ህፃናት ጀምሮ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ ዕደ ጥበብ ሥራና በተለያየ ሙያ ታንፀው እንዲወጡ ለታራሚዎች እየተደረገ ያለው ሥራ ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና በመስክ ምልከታ በተሳተፉ አካላት ተገልጿል።

በአጠቃላይ የታራሚዎች አያያዝና ማረምና ማነፅ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ ሆኖ ማግኘታቸውን የምክር ቤቱ፣ ህግና ፍትህ መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዱንጋ ናኩዋ ገልፀዋል።

በታራሚዎች የሚመረቱ የተለያዩ የሙያ ሥራዎች መሸጫ ቦታ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ተሞክሮ የሚወሰድና የግብርና ሥራ ለማምረት የመሬት አቅርቦት ችግር እና በሌሎችም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን አስፈፃሚ አካላት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አቶ ዱንጋ ገልፀው ምክር ቤቱም ይህ እውን እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።

በተወሰነ መልኩ በአንድ ክፍል የታራሚዎች መኝታ ክፍል ላይ ጥበት በመኖሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የመኝታ አገልግሎት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ግብረ መልስ ተሰጥቷል።

ተቋሙም የተነሱ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚሠራና ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች እንዲፈቱ ምክር ቤቱ ሚናውን እንዲጫወት ተጠይቋል።

የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ የተመራ ህግና ፍትህ መልካም አስተዳደር ፣ ማህበራዊ ዘርፍ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተቋሙ የታራሚዎች አያያዝና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን