በሆሳዕና ከተማ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የተገነባው ”ሳሚ ሆቴል” በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በምረቃው ፕሮግራም ንግግር ያደረጉት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል በከተማው በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ሳይሰራ መቆየቱን አስታውሰው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መነቃቃቶች መኖራቸውን ተናግረዋል::
በተለይም በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችና ጎብኚዎች የተሻለ አገልግሎት አግኝተው እንዲመለሱ ለማስቻል በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ማገዝ የአካባቢን ልማት መፋጠን እና የስራ አጥ ቁጥርን መቀነስ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የ”ሳሚ ሆቴል” ባለቤት ዳኛ መኮንን ተሰማ በምረቃው ወቅት እንዳሉት በብዙ ጥረት ሆቴሉ አሁን ላለበት ደረጃ መብቃቱን ገልፀው ለግንባታውም ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
የሆቴሉም መገንባት ለከተማው ገፅታና ለእንግዶችም አማራጭ ማረፊያ በመሆን የራሱን ሚና እንደሚወጣ የገለፁት የሆቴሉ ባለቤት ከ40 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ባለ 4 ወለሉ የ”ሳሚ ሆቴል” በ6 መቶ ካሬ መሬት ላይ ያረፈና በውስጡም ከ30 ባላይ የመኝታ ክፍሎች፣ ባርና ሬስቶራንት፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራና ሌሎች አገልግሎቶችን ያሟላ ነው ያሉት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ባፋ ናቸው።
በወቅቱ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው ኢንቨስትመንት ለአንድ ሀገር ዕድገት መፋጠን ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ የዞኑ መንግሥት በአካባቢው የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፀጋዎችን በተገቢው መጠቀም እንዲቻል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ባለሀብቶች ከውሃ፣ ከመብራት ከመንገድ ጋር አያይዘው የሚያነሱ ችግሮችንና ውስንነቶችን ለመቅረፍ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ