በተፈጥሮ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ህጻናትና ልጆች ነጻ ህክምና አገልግሎት ተሠጠ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቦንጋ ገ/ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል በተፈጥሮ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ህጻናትና ልጆች ነጻ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በተደረገላቸው ነጻ ህክምና መደሰታቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
ትረስት የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ከሆስፒታሉ ጋር በመተባበር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች ለተውጣጡ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የነጻ ህክምናውን ተደራሽ አድርጓል።
የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ይህ ነው የተባለ ትክክለኛ ምክንያት ባይኖረውም ከዘር ወይም ከቤተሰብ፣ ተመሳሳይ ችግር ካለ በዕርግዝና ወቅት የሚወሰዱ መድሀኒቶችና ሌሎች ለችግሩ መንስኤ ለሆኑ እንደሚችል ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የላንቃ መሰንጠቅ ላጋጠማቸው ህጻናት በበቂ ሁኔታ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አለመኖራቸውና ለህክምናው ወጪ በበቂ ደረጃ ባለመኖሩ ምክንያት በርካቶች ሲቸገሩ ቆይተዋል።
ትረስት የበጎ አድራጎት ድርጅትም ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱ የኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫናዎችን ለማስቀረት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመዘዋዋር በዘርፉ የህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ነጻ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የማህበሩ መስራችና ዳይሬክተር አቶ ደሴ ዳቼ ተናግረዋል።
በዚህም ከ 1ሺ 800 በላይ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በተመባበር አገልቱን በቅርበትና በስፋት ለመስጠት እንቅስቃሴዎች እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
የቦንጋ ገ/ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረማርያም ጳውሎስ የተሰጠው አገልግሎት በሆስፒታሉ በመደበኛነት ይሰጡ ከነበሩ አገልግሎቶች በተለየ መልኩ የችግሩ ተጋላጮችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
በሆስፒታሉ የነጻ ህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ከዳውሮ ዞን የመጡት ወይዘሮ ሊያ ባሳ እና ከካፋ ዞን ሺሾንዴ ወረዳ የመጡት አቶ ወርቁ ገ/ስላሴ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ መሉ የትንስፖርት እና የህክምና ወጪያቸውን ሸፍኖ ለልጆቻቸው በሰጠው የህክምና አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ስለ ከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ግንዛቤ እንደሌላቸውና በህክምና የሚስተካከል መሆኑን እዳልተረዱ የገለጹት ተገልጋዮቹ፥ ድርጅቱ ከብዙ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች እንዳላቀቃቸውም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በቀጣይ ህክምናውን በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎች የችግሩ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ