በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የዋቸሞ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በ126.7 ሚሊዮን ብር ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አስታወቀ

በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የዋቸሞ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በ126.7 ሚሊዮን ብር ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አስታወቀ

ትምህርት ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከቀድሞ ተማሪዎች፣ ከሆሳዕና ከተማ፣ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከባለሀብቶች ጋር ውይይት አካሄዷል።

የዋቸሞ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታምሬ ኩራሴ ለውይይት የሚሆን መነሻ ሀሳብ ባቀረቡት ወቅት እንደገለጹት የቀድሞ ልጅ አበበ ወ/ሰማያት የአሁኑ ዋቸሞ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በ1964 ዓ/ም ከተመሠረተ ወዲህ የአገር መሪዎችንና ሳይንስስቶችን ጨምሮ በርካታ ምሁራን አፍርቷል።

ትምህርት ቤቱ በትውልድ ቅብብሎሽ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ሁኔታ ላይ ቢደርስም ቤተ መጽሐፍቱ ከተማሪ ቁጥር ጋር ስነጻጸር የማይመጥን ሆኖ በመገኘቱ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት መወሰኑን አቶ ታምሬ ጠቅሰዋል።

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ ዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የቤተ መጽሐፍቱን ዲዛይን አለም የደረሰበትን ደረጃ በሚመጥን መልኩ አዘጋጅቶ የሰጠ ሲሆን ከቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ባለፈም የቪዲዮ ኮንፈረንስና የመዝናኛ አገልግሎትም ይሰጣል ብለዋል።

ግንባታው በ3 ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን 126 ሚሊዮን 780ሺህ 272 ብር በጀት ይፈልጋል ።

ለግንባታው ዕውን መሆን በአገር ውስጥና ውጭ አገር የሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ባለሀብቶችና ማሕበረሰብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ያናጋገርናቸው የትምህርት ቤቱ መምህራን በበኩላቸው የዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ መገንባት በተቋሙ እየተስተዋለ ያለውን የቤተ መጽሐፍት ጥበት ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳለቸው ገልጸዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተደደር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት አቅደው ወደ ተግባር መግባቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረው እንደ አንድ የቀድሞ ተማሪ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የከተማው አስተዳደሩም ፕሮጀክቱ ግብ እንድምታ ሀላፊነት እንደሚወስድ ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፡ ጌታቸው መጮሮ -ከሆሳዕና ጣቢያችን