በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በካፋ ዞን በግብርና ስራዎች ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፈው በጀት ዓመት በግብርና ስራዎች ውጤታማ እንቅስቃሴዎች መመዝገባቸውን የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ለዞኑ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ገለጹ።
ዋና አስተዳዳሪው የአስፈጻሚ ተቋማትን የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
ዋና አስተዳዳሪው በሪፖርታቸው በክረምት እርሻ 121 ሺህ 965 ሄክታር ማሳ በዋና ዋና ሰብሎች መሸፈኑን ጠቁመው፥ ከዚህም ወደ 2 ሚሊየን 720 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ከታቀደው 2 ሚሊየን 236 ሺህ ያህሉን ማሳካት እንደተቻለ አመላክተዋል።
ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር በአመቱ በአጠቃላይ 54ሺህ 604 ሄክታር ማሳ የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 15 ሸህ 62 ሄክታር በሙሉ ፓኬጅ የተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር ውስንነት መኖሩን በሪፖርቱ አሳይተዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሰብሎች ላይ የሚደርሱ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር መከናወኑንና የአፈር ማዳበርያ አጠቃቀም 46 ኤን.ፒ.ኤስ.ቢ እና 40 ሺህ ዩሪያ የአፈር ማዳበርያ ቀርቦ አገልግሎት ላይ መዋሉን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
የኩታ ገጠም እርሻ ሥራ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር በስፋትና በጥራት ለማከናወን በተደረገው ጥረት በክረምቱ የእርሻ ወቅት ከ11 ሺህ 735 ሄክታር ማከናወን መቻሉን የገለጹት አቶ እንዳሻው፥ እርሻን በማዘመንና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
ከተለመደው የአስተራረስ ዘዴ በመውጣት የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ለማላመድ በተደረገው ጥረት ከ8 ሺ 920 ሄክታር በላይ ማከናወን የተቻለበት ወቅት ነው ብለዋል።
በ2017 የበጋ እርሻ ወቅት 142 ሺህ 553 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 95 ሺ 357 ሄክታር ማሳ በማዘጋጀትና በዘር ለመሸፈን ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አቶ እንዳሻዉ አብራርተዋል።
በአንደኛና ሁለተኛ ዙር የመስኖ ሥራ በሙሉና በከፊል ፓከጅ እንዲሁም በልማዳዊ አስተራረስ ከ17 ሺህ 500 በላይ ሄክታር ማሳ በማልመት ከ3 ሚሊየን 920 ሺህ 500 በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
የዞኑ ህዝብ ዋነኛ የምግብ ምንጭ የሆነውን እንሰት ምርት ለማሳደግ የዘር ብዜትን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ ከ78ሺህ 143 ሄክታር ማድረስ የተቻለ ሲሆን ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን በሪፖታቸው የገለጹ ሲሆን፥ በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት እየቀረበ ነው።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
በመንግስትና በፓርቲ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዘገቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የብልፅግና ህብረት ፓርቲ አመራርና አበላት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አከናወኑ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በኮላንጎ ከተማ እያካሄደ ነው