የባስኬቶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም በጀት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

የባስኬቶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም በጀት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የባስኬቶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የቀረበለትን 600 ሚሊዮን 667 ሺህ ብር የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የዞኑ ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

የተበጀተው ውስን የመንግስት ሐብት ለታለመለት አላማ ብቻ ይውል ዘንድ አስፈጻሚ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።

የባስኬቶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወዳጆ ገነሞ የተመደበው በጀት ከመንግሥት ግምጃ ቤት 300 ሚሊዮን 251 ሺህ 887፣ ከመደበኛ ገቢ 242 ሚሊዮን 350 ሺህ 794፣ከጤና ተቋማት ገቢ 12 ሚሊዮን 24 ሺህ 438ብር፣ ከትምህርት ቤቶች ገቢ 5 ሚሊዮን 769 ሺህ 881 ብር እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 40 ሚሊዮን 280 ሺህ 154 የሚገኝ መሆኑን ባቀረቡት ዕቅድ አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው በጀት ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን በተለይ የውስጥ ገቢን አሟጦ መሠብሠብ ከምንግዜውም በላይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አመላክተዋል።

በዞኑ የሚመረቱ የውጪ ገበያ የቅባትና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ከህገ ወጥ ንግድ በመከላከል ወደ መንግስት ካዝና መግባት የሚገባው ገቢ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የተመደበውን ዉስን በጀት ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬው ፍሻለው በሠጡት ማብራሪያ በጀቱ ሲሸነሸን ቅድሚያ ለሠብአዊ ጉዳዮች በተለይም ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በመቀጠልም ከህዝቡ ለሚነሱ መሠረታዊ የመልማት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቶት የተመደበ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተመደበው አጠቃላይ በጀት 22 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለካፒታል ዕድገት ተግባራት እንዲውል መደረጉንም በሠጡት ምላሽ አብራርተዋል።

የባስኬቶ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ክፈለው በለጠ በበኩላቸው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ ግዢዎች ለአብነትም የተሽከርካሪ ግዢ በዞን ደረጃ የማይፈጸም መሆኑን፥ የበጀት ኮድ በሌለው ቦታ ላይ ምንም ገንዘብ መመደብ በየትኛውም አግባብ ተቀባይነት እንደማይኖረው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን