በዕውቀት የተካነ ትውልድ ለሀገር ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ

በዕውቀት የተካነ ትውልድ ለሀገር ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዕውቀት የተካነ ትውልድ ለሀገር ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለፁ።

የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ በመደበኛ መርሃ ግብር በዲፕሎማና በሰርትፊኬት ያሠለጠናቸውን 5 መቶ 59 ተማሪዎችን ለ19ኛ ጊዜ አስመርቋል።

ኮሌጁ ከተቋቋመበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ከ37 ሺህ 6 መቶ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች በማሠልጠን ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ማሠማራቱ በመድረኩ ተገልጿል።

የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ አካዳሚ ምርመር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን እና የዲኑ ተወካይ አቶ ተካ ሞጬ በምረቃው ፕሮግራም ባደረጉት ንግግር፤ ኮሌጁ የመማር ማስተማር ስርዓትን በማጎልበት የዕውቀትን ብርሃን ሲያፈካ መቆየቱን ተናግረዋል።

አቶ ተካ አክለውም፤ የትምህርት ጥረትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ማለትም የቤተ መጽሐፍት፣ የቤተ ሙከራ፣ የኮምፒውተር እና ሌሎች የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ተግባራት በኮሌጁ ትኩረት የተሠጠቸው ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በኮሌጁ ቆይታ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቂ ዕውቀት የቀሰሙ በዲፕሎማ 148 ሴት እና 189 ወንድ እንዲሁም በሰርተፊኬት 18 ወንድና 209 ሴት ዕጩ መምህራን በዕለቱ ለምረቃ መብቃታቸውንም ምክትል ዲኑ አስተውቀዋል።

በምረቃው ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ተግዳሮት ለመሻገር ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ላይ እየተሠራ ባለው የሪፎርም ሥራ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱን አቶ አንተነህ ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ ከኮሌጁ የቀሰሙትን ዕውቀት በመልካም ስነ ምግባር አንጸው ለማህበረሰቡ እንዲያበረክቱም ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ዮርዳኖስ መስቀሉ እና ቢንያም ኃይሌ በከፍተኛ ማዕረግ መመረቃቸው በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልፀው፤ በተቋሙ ቆይታ ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ለማዋል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በዕለቱም ተቋሙ በ49 ሚሊዮን 2 መቶ 50 ሺህ ብር ያስገነባው 24 የመማሪያ እና 10 ቢሮዎችን የያዘ ባለ 3 ወለል ህንፃ የተመረቀ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ተከናውኗል።

ዘጋቢ፡ መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን