በኮሌጁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በተለያዩ የሙያ መስኮች በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን በስልጤ ዞን የሳንኩራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አስታወቀ
ኮሌጁ አደራጅቶ ወደ ስራ ያስገባቸው ሰልጣኞች በተመቻቸላቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የሳንኩራ ኢንዱስትሪያል እና ኮንስትራክሽን ኮሌጅ ስራ ከጀመረበት 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን እያሰለጠነ ከዘርፉ የሚጠበቀውን የሰው ኃይል በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም በመደበኛና በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ሰልጣኞችን ተቀብሎ እያሰለጠነ መሆኑን የኮሌጁ ዲን አቶ ሙስጠፋ ሸምሰዲን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በዘጠኝ የሙያ ዘርፎች ሰልጣኞችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሙያ መስክ ሆኖ በመጣው የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት 2 ሺ 50 ሰልጣኞችን እያሰለጠነ ይገኛል።
ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺ 7 መቶ 50 ያህሎቹ ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ መሆናቸውን አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል።
ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ለዘርፉ ተፈላጊውን የሰው ኃይል ከማፍራት በተጨማሪ በኮሌጁ ስልጠናቸውን ተከታትለው ላጠናቀቁ ሰልጣኞች በተለያዩ የስራ መስኮች አስራ ሰባት አባላት ያሉበትን ሶስት ማህበራት በማደራጀት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀዋል።
በወተት ተዋጽኦ፣ በከብት ማደለብ፣ በእንጨትና ብረታብረት እንዲሁም በአውቶሞቲቭ ስራ ተደራጅተው ወደ ስራ ያስገባቸው እነዚህ ሰልጣኞች መስሪያ ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ የስራ ማስጀመሪያ የሚሆን በጀት 5 መቶ ሺ ብር ብድር በኮሌጁ በኩል እንደተመቻቸላቸው ዲኑ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አምስት ለሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ሰልጣኞች ኮሌጁ መኖሪያ ቤት በማመቻቸት ስልጠናቸውን እንዲከታተሉ እያደረገ ሲሆን ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ በኮሌጁ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ዕቅድ መያዙን አቶ ሙስጠፋ ገልፀዋል።
መምህር አስራር ሙክታር በኮሌጁ ሜካኒካል ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆን ኩሪ ታደሰ ደግሞ የሆቴል ቱሪዝም መምህርት ናቸው።
እንደየትምህርት ክፍላቸው ሰልጣኞች በኮሌጁ በሚኖራቸው ቆይታ ለዘርፉ ተፈላጊ የሆነ ብቁ እና ተወዳዳሪ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኮሌጁ ሰልጣኞች የተግባር ስልጠና የሚያገኙበት ቁሳቁስ የተሟላ በመሆኑ ሰልጣኞች በተግባር በሚሰለጥኑበት ወቅት የተሟላ ዕውቀትና ልምድ እንደሚያገኙ የኮሌጁ መምህራን ገልፀዋል።
በኮሌጁ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ እና አጠናቀው በተለያዩ የስራ ዘርፎች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሰልጣኞች እንደገለፁት በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ ተወዳዳሪ እና ስራ ፈጣሪ የሚያደርጋቸውን ክህሎት መቅሰም ችለዋል።
ስልጠናቸውን አጠናቀው ኮሌጁ በተለያዩ የስራ ዘርፎች አደራጅቶ መነሻ የብድር ድጋፍ በማቅረብ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሰልጣኞች በአሁኑ ሰዓት በሚያገኙት ገቢ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም በሙሉ ድምፅ ፀደቀ
የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለፀ
የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፍትህ እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረቱ ጥሪ አቀረቡ