የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም በሙሉ ድምፅ ፀደቀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም በሙሉ ድምፅ ፀደቀ

ሀዋሳ: ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ውሎ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አፈፃፀም እና የ2018 የበጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የክልሉን ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ አደም፥ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የኦዲት ሪፖርት እንደገለጹት፥ የክልሉ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ውስን የሆነውን የህዝብና የመንግስት ሀብት፥ የፋይናንስን ህግና አሰራር ተከትለው እንዲሰሩ ለማስቻል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ የምክር ቤቱ አባላት የሰጡት አስተያየት ተቋሙ በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ ግብዓት እንደሚሆን አመላክተዋል።

የመንግስትን ውስን ሀብት ከብክነት ለመጠበቅ ህጋዊ አሰራሩን ተከትሎ ስለመፈፀሙ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወኑን የጠቆሙት ዋና ኦዲተሯ፥ የገቢ፣ የፋይናንስና ህጋዊ ኦዲት፣ የክዋኔና አካባቢ ኦዲት፣ የልዩ ኦዲት ስራዎችን መሰራቱን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ኦዲት ከተደረጉ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የገቢ አሰባሰባቸው፣ የበጀት አጠቃቀማቸው፣ የሂሳብ አያያዛቸው እና የንብረት አስተዳደራቸው ከወጡ ህጎች አንጻር መፈተሹንም ገልፀዋል።

የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ማረምና የውስጥ ኦዲትን ማጠናከር ይገባል ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፥ የኦዲት ግኝቶችን በዘላቂነት ማስተካከልና በኦዲት ግኝት ላይ በተስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2017 በጀት አመት አፈፃፀም፣ የ2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ እንዲሁም የበጀት ረቂቅ ቀርቦ በምክር ቤት አባላት ሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ