የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር በ2017 ዓ.ም የስራ ክንውን አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓመተ ምህረት ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።

በጉባኤው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ማልደዮ፤ የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ተኪ የሌለው ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በሀገራችን የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ ተቀርጾ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም ወደሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱንም አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።

መንግስት ስር የሰደደውን የትምህርት ጥራት ችግር በጥናት በመለየት አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፍኖታ ካርታን ቀርጾ እንዲተገበር በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመምህራን አቅርቦት፣ ለመምህራን የትምህርት ደረጀ ማሻሻያ እና የማስተማር ስነ-ዘዴ ስልጠና በመስጠት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሳደግ፣ አዳዲስ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ነባር ትምህርት ቤቶችን የማደስ፣ የመማሪያ መጽሐፍት የማቅረብና የመምህራን መብትና ጥቅማጥቅም ለማስከበር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ ማቲዎስ አብራርተዋል።

መምህራን በሙያቸው ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ከማፍራት በተጓዳኝ በራሳቸው ተነሳሽነት የምርምርና ጥናት ስራዎችን በመከወን ለሀገር ዕድገት ጉልህ ሚና እየተወጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

መምህራን ለሀገር ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ በተነቃቃ መንፈስ ስራቸውን ወደው እንዲሰሩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን መቅረፍ የሚችሉ የጥቅማ ጥቅም እና የማበረታቻ ተግባራት መተግበራቸውንም አቶ ማቲዎስ አንስተዋል።

የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ በመምጣቱ በ8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች በሚሰጠው ፈተና 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅ እያለ መጥቷል ብለዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን ለ8ኛ ክፍል ፈተና 18.5 በመቶ እና ከ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 2.7 በመቶ ብቻ 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ማምጣታቸውን ጠቁመው በ2016 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ወደ 44 በመቶ የ12ኛ 3.4 በመቶ ማደጉንም አውስተዋል።

በጉባኤው የተገኙት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት እና የአለም መምህራን ማህበር ቦርድ አባል ዶክተር ዮሃንስ በንቲ ጉባኤው ያስፈለገበት ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በማህበሩ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገምና የልማት ሁሉ ቁልፍ የሆነውን የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ለማስቀመጥ፣ የቦርድ አባላት ምርጫ እና የቀጣይ 4 ዓመታት የስራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ለትምህርት ጥራትና ለመምህራን ጥቅመ ጥቅምና መብት መከበር የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ በመቀጠል ለትውልድ ግንባታ በትምህርት ዘርፍ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት በተዘጋጀው መድረክ ከትምህርት ጥራትና መምህራን ጥቅማ ጥቅምና መብት ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጡንም ዶክተር ዮሃንስ አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ በርታ ያረቢ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት በተከተለ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጉባኤው እስካሁን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል በተከናወኑ ተግባራት የመጡ ለውጦችና ያልተፈቱ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በዝርዝር የዳሰሰ ሰነድ እና የፋይናንስ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለ4 ዓመታት ማህበሩን የሚመሩ አመራር አካላት መመረጣቸውም ተመላክቷል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን