የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፍትህ እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረቱ ጥሪ አቀረቡ
በፕሬዝደንቱ የተመራ ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳውላ ከተማ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥን ጉብኝት አካሂዷል።
በኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት በአቶ ቴዎድሮስ ምህረት የተመራ ልዑክ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሣዉላ ከተማ ሲደርሱ በክልልና በዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በሐገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልክታቸው የጎፋ ዞን በእምቅ የተፈጥሮ ሀብቶቿ የምትታወቅ አካባቢ ስትሆን ይህንን ሀብት ወደ ሀብት ለመቀየር በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ አወቃቀር ልዩ ዕድል ማግኘቷን ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ፤ በሀገሪቱ ያሉ የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ትብብር አስፈላጊነቱ በህጎች አተረጓጎም ግጭት እንዳይፈጠር ከማድረግ አንፃር ፋይዳዉ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የዳኝነት አካሉን አቅም በማጎልበት የተሟላ ቁመና ያለዉ ባለሙያ እንዲፈጠር ከማስደረግም አንፃር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለክልሎች ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ተቋማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ እያደረገ ያለዉ ድጋፍ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ በሐገር አቀፍ ደረጃ የዳኝነት ዘርፉን በማዘመን የዜጎችን የፍትህ ፍላጎት ለማጎልበት የ3 አመት ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው ይህ ጉብኝትም አፈጻጸሙ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍትህ ተደራሽነቱን እውን ከማድረግ አኳያ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዘርፉ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፍትህ እንዲሰፍን ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ፕሬዝደንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ልዑካኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በኮሌጁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በተለያዩ የሙያ መስኮች በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን በስልጤ ዞን የሳንኩራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም በሙሉ ድምፅ ፀደቀ
የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለፀ