የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና፣ በሰብል ልማት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የባለ ብዙ ፀጋዎች ባለቤት ነው – አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር)

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና፣ በሰብል ልማት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የባለ ብዙ ፀጋዎች ባለቤት ነው – አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር)

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና፣ በሰብል ልማት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የባለ ብዙ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

‎በቂና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ለኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት ለማዋል ለግብርና ስራ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ተብሏል።

‎በወቅቱ የማምረቻ ሼድ፣ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ምረቃ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማት የምክክር መድረክ ተከናውኗል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ብርሀኑ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እንዳሉት፤ “የክልሉን ፀጋና ሀብት ወደ ላቀ ኢንዱስትሪ ልማት” በሚል መሪ ቃል በርካታ ኩነቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

‎የዛሬውን ኤግዚቢሽን እና ባዛር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማት የምክክር መድረክ የክልሉን ፀጋ በማወቅና በመረዳት ለላቀ የኢንዱስትሪ ልማት ለመጠቀም በቅንጅት መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።

‎በክልሉ 9 ከተሞች፣ በ17 የኢንዱስትሪ ክላስተር ማዕከላት፣ በ119 ብሎኮች፣150 ሼዶች እና 126 ኢንተርኘራይዞች በልዩ ልዩ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ጥላሁን።

እነዚህ የኢንዱስትሪ ክላስተሮች ከ2 ሺህ 900 በላይ አዳዲስ የስራ እድሎች ከመፍጠራቸው ባሻገር የተጠናከረ የገበያ ትስስር፣ ተኪ ምርትና ኤክስፖርት ላይ በስፋት በመስራት የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተከናወነባቸው እንደሆነም አውስተዋል።

‎በቂና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ለኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት ለማዋል ለግብርና ስራ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብንም ሲሉ አሳስበዋል ስራ አስፈፃሚው።

‎የመካከለኛ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ስራዎችም በዲላና ይርጋጨፌ እየተከናወኑ ሲሆን ለአብነትም በዲላ ሲዝ አግሮ ፒ ኤል ሲ የተባለ ካምፓኒ በሁለት አመታት ውስጥ ከ50 ቶን በላይ ድፍድፍ የአቮካድ ዘይት ለውጪ ገበያ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

‎መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር)፤ መንግስት በተለያዩ ከተሞች የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ክልሉ በግብርና፣ በሰብል ልማት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የብዙ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቀጣይም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የኤክስፖርት ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበው፤ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን አቅም ከማሳደግ ባሻገር ከአቅም በታች እያመረቱ የሚገኙትን በጋራ የመደገፍ ስራ ይሰራል ብለዋል።

‎በመርሀ ግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አበባዬሁ ታደሰ (ዶ/ር) ጨምሮ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አዳማ ትምጳዬ፣ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢተው፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እና ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ናቸው።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን