በተጠናቀቀው በጀት አመት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ

በተጠናቀቀው በጀት አመት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ

ሀዋሳ: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው በጀት አመት የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት የነበረውን የመንግስት ሥራ አፈፃፀም በዝርዝር በመገምገም እና በሂደቱ የነበሩ መልካም ልምዶችን በመቀመር ይበልጥ መረባረብ የሚያስችል የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ገልፀዋል፡፡

የክልሉን የ7 ዓመታት ስትራተጂክ ዕቅድ እና እምቅ የሆነ የመልማት አቅምን ያገናዘበ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ በሚያስችል አግባብ ርብርብ መደረጉን አመላክተዋል፡፡

ለአፈፃፀም መሻሻል አንዱ መነሻ ትክክለኛ ዕቅድ በመሆኑ በዕቅድ ዝግጅት ወቅት በተለይ በየዘርፉ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው ያገናዘበ ዕቅድ በማዘጋጀት መላው አመራር፣ የመንግስት ሠራተኛው፣ በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ አደረጃጀቶች፣ በአጠቃላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዕቅድ ዙሪያ እንዲመክሩ በማድረግ ሁሉም ተዋናዮች ተግባቦት ፈጥረው ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡

በሁሉም አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የታቀዱ ተግባራትን ለማሳካት በመደበኛነት እየተደረገ የነበረ እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በ2016 በጀት ዓመት እንደተደረገው ሁሉ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ቁልፍ ተግባራት በሚል የተለዩት የሰላም ግንባታ ሥራ፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ገቢ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ማረጋጋትና የከተማ ኮሪደርና የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ሥራዎች፣ እና በሁሉም ተቋማት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በልዩ ትኩረት እንዲመሩ መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ አንዱ እና ጉልህ ተግባር ተደርጎ የሚወሰደው በሰባቱም የክልል ማዕከል ከተሞቻችን የክልል መንግስትነትን መሰረት ለመጣል የሚያስችሉ ግዙፍ የሆኑ የቢሮ፣ የአዳራሾች እና የቤተመንግስት ግንባታ ሥራ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት በመመደብ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው፥ የክልሉ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ የሕዝቡ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ