ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ልዩ አርማ ሆኖ በታሪክ አሻራ ይመዘገባል ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገለፁ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ልዩ አርማ ሆኖ በታሪክ አሻራ ይመዘገባል ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገለፁ

የህዳሴ ዋንጫ ተረኛ ተረካቢ የሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን ከኣሪ ዞን በተረከበበት መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ነው የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በህብረት ችለናል እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም ዋና አስተዳዳሪው ለታዳሚው አስተላልፈዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከህዝብ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት ከማሟላት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንት ዘርፍና በሁሉ አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት አቅም በመፍጠር እና የመላው ኢትዮጵያዊውን አንድነትን በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

እንደ ዞን 22 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር በላይ በግድቡ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አቶ ማዕከል ገልፀዋል።

በድጋፍ ማዕቀፍ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ዋና አስተዳዳሪው አመስግነዋል።

በቅርቡ ግድቡን አስመርቀን ኢትዮጵያዊያን በህብረት እንደሚችሉ በዓለም ህዝብ እናስመሰክራለን ሲሉም አቶ ማዕከል ገልፀዋል።

የህዳሴ ዋንጫውን ለሳምንት ያህል ቆይታ ካደረገው ከኣሪ ዞን ተረኛ ለሆነው ለደቡብ ኦሞ ዞን ለማስረከብ በመርሐ ግብሩ የተገኙት የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ከተማና መሠረተ ልማት መመሪያ ሀላፊ አቶ ገረመው ኃ/ማርያም እንደገለፁት፤ ግድቡ በኢኮኖሚ ራሳችንን እንድንችል የብልጽግና ማሳያ ነው።

የዲመካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወሌ አልማ፤ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት በዓለም አደባባይ የትኛውንም ግዙፍ ልማት በራስ አቅም ማከናወን እንደምንችል በተግባር አሳይተናልና በዚህም ልዩ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።

በቀጣይም ከዚህ የሚበልጥ ትላልቅ ልማቶችን እውን እንደምናደርግ አንድነታችን በራሱ ይመሰክራል ሲሉም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተማ አስተዳደሩ አርብቶ አደሩንና የከተማውን ነዋሪ፣ መንግስት ሠራተኞችን እና የተለያዩ አካላትን በማነቃነቅ ለግድቡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልፀው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን