ወጣቶች የነገ ለምለምና ውብ ሀገርን ለመረከብ ከአካባቢ ጀምሮ በበጎ ተግባራት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተጠቆመ

ወጣቶች የነገ ለምለምና ውብ ሀገርን ለመረከብ ከአካባቢ ጀምሮ በበጎ ተግባራት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተጠቆመ

የጎፋ ዞን ደምባ ወረዳ ወጣቶች የ2017/18 ክረምት የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በወረዳው ቦላ ቀበሌ ችግኝ የመትከል ስራ በማስጀመር በተለያዩ መስኮች ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ሊወጣ ያለ ገንዘብ ለማዳን መታቀዱ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ ”በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በክረምት በጎ ፈቃድ ስራ ከ16 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ 43 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ከመንግስት ካዝና ሊወጣ ያለውን ገንዘብ ለማዳን መታቀዱን አስረድተዋል።

ወጣቶች ”ሁለት መቶ ብር ለእናቴ” በሚል ሀሳብ በወሊድ ወቅት በደም እጦት ለሚሰቃዩ እናቶች ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ መጀመራቸው የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ክረምት ዕድሮች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና በወጣቶች 60 ነባር እና አዲስ የአረጋዊያን ቤት ግንባታ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አራሹ አበበ፤ ወጣቱ በሀገራዊ ኢንሼቲቭ ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለው እያንዳንዱ ቀበሌ ከ1 ነጥብ 5 ሄክታር በወረዳ ደረጃ ከ30 ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ወጣቱ የነገ ለምለምና ውብ ሀገርን ለመረከብ አሁን ከሚመራው መሪና ህዝቡ ጋር በመተባበር ከአካባቢ ጀምሮ ማልማት እንዳለበት አንስተው፤ በችግኝ ተከላው ላይ እንደተሳተፉ እስከ አገልግሎት ድረስ መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የጎፋ ዞን ወጣቶች ፌደሬሽን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ኤሊሮኢ አላዛር እና የቀበሌው ደጋፊ አመራር አቶ ቱጃሬ ቱሩንጎ፤ ወጣቶች አረንጓዴ አሻራ ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን አንስተው ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች እየተተከሉ ነው ብለዋል።

የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የወጣት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳጋራ፤ በወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ ከ15 ሺህ በላይ ችግኝ መትከል፣ የአረጋውያን ቤት ግንባታ፣ 40 ዩኒት ደም ልገሳ እና በሌሎች የትኩረት መስኮች ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል።

በበጋ በጎ ስራ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ ብርቱ ተሳትፎ በማድረግ የወረዳውን መንግስትና ህዝብን በማስተባበር ከ250 ሺህ ብር ገቢ በማሰባሰብ የአንዲት አቅመ ደካማ እናት በከባድ ቆዳ በሽታ የሚሰቃዩ ሁለት ልጆቿን ህክምና እንዲወስዱ ማድረጋቸው በተሞክሮ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወይዘሮ በረከት ወዛ በክረምት ወራት እናቶች ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ ማስተማር፣ የማህፀን ጫፍ በር ካንሰር የግንዛቤ ስራን ጨምሮ በ11 ትኩረት መስኮች በጎ ተግባራት የሚከናወኑ መሆናቸውን አስረድተው ለአቅመ ደካማ እናቶች ድጋፍ የሚሆን እስከ 60 ሺህ ብር ገንዘብ ማሰባሰብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ ወጣቶች ዘንድሮ በጎ ስራዎችን ሰርተን ማለፍ ብቻ ሳይሆን የክትትል ስራዎችን በትኩረት ለማከናወን ቃል እንገባለን ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን