የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ

የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ

ቢሮው ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ በ64 ሚልዮን ብር በሆነ ወጭ 13 ኪሎ ሜትር ዛዝኤ-ካምኣሌ ባርኤ ኦሮ-ዛላ ዶላ የገጠር ትስስር መንገድ አስጀምሯል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃ/ማሪያም ተሰፋዬ በመንገድ ማስጀመሪያ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት በየደረጃው የህዝብን መሠረት ልማት ችግር ለመፍታት እየሰራ ይገኛል።

ክልሉ በርካታ ፀጋዎች ያሉበት ቢሆንም በቂ የመንገድ መሠረት ልማት ዝርጋታ ባለመኖሩ በተለይ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጉን ገልጸዋል።

ቢሮው ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ ዛዝኤ-ካምኣሌ ባርኤ ኦሮ-ዛላ ዶላ የገጠር ትስስር መንገድ ሥራ በይፋ ማስጀመሩን ገልፀዋል።

መንገድ በ64 ሚልዮን ብር በሆነ ውጭ የ13 ኪሎ ሜትር በስድስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን የገለፁት አቶ ኃ/ማሪያም፤ መንገዱን ኮንትራክተሩ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲያጠናቀቅ አመራሩና ህብረተሰቡ በቅንጅት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምሴ አድማሱ በበኩላቸው፤ ዞኑ የመሠረተ ልማት ቁልፍ የሆነውን የመንገድና የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በዞኑ ገረሴ ዙሪያ ወረዳ አራት ቀበሌያትን የሚያገናኘው መንገድ ሥራ መጀመሩ በአካባቢው የሚገኘው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠቀም እንደሚያስችል ገልፀው፤ መንገድ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቀ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የገረሴ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ቦርሴ ቦተ የረጅም ጊዜ የህዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የዛዝኤ-ካምኣሌ ባርኤ አሮ-ዛላ ዶላ መንገድ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው መንገድ ባለመኖሩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ መቆየታቸውን ተናግረው መንገድ በመጀመሩ በእጅጉ መደሰታቸውንም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ አለሚቱ አረጋ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን