የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ ሀብት ማፍራት ለመቀየር ያለመ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ገለፀ
ቢሮው፤ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት የ2017 ዓ.ም አፈፃፀምና ፕሮጀክት አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት ከተረጂነት ወጥተው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ላይ ያለመ ሰው ተኮር ፕሮግራም ነው።
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ ሀብት ማፍራት ለመቀየር ያለመ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ሥራውን ለማሳለጥ በጥራት በማቀድና በማስፈፀም የተጠናከረ ክትትልና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተፈሪ አባተ እንደገለፁት፤ ፕሮግራሙ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት በመሆኑ ለተጠቃሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የከተሞች የማስፈፀም ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ የምስራች ገመዴ፤ በክልሉ በስድስት ከተሞች ላይ ከዚህ ቀደም በተደረገው ግምገማ በከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቅሰው በወቅቱ በጥንካሬና በጉድለት የተለዩ ነጥቦችን ለማስቀጠልና ለማረም የተዋቀሩ ስትሪንግ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አክለውም ሥራው እንዲቀላጠፍ ከግብዓት አቅርቦትና ጥራት አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ በበኩላቸው፤ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተጀመረ አንስቶ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ጠቁመው፤ ፕሮግራሙ ከሚሰጠው ፋይዳ አኳያ በጉድለት የሚነሱ ጉዳዮችን ማጥራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ፤ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በአለም ባንክ በሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ዓላማውም በከተሞች በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን በዘላቂ ሁኔታ ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ከመድረኩ ተሣታፊዎች መካከል የሳውላ ከተማ ከንቲባ ንጉሴ መኮንን(ዶ/ር) እና የዲላ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ ዕድል ፈጠራና እንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ፤ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማደግ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ጠቁመው ፕሮግራሙ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና የአመራር ማዕቀፍ የሚጠይቅ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳዳርና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ተፈሪ አባተ፣ የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሣትፈዋል።
ዘጋቢ: አስናቀ ካንኮ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ተጠናቀቀ
የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ
የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ የሆነው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በራስ አቅም የመቻላችን ምልክት ነው ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሮች ተናገሩ