ለገጠር ኮሪደር ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
በክልሉ ዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ በአሩሲ ሞጊሲ ቀበሌ የአርሶ አደር ዳመነ ወላንቾ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጋሾ እንደገለጹት፤ በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች የዜጎችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በህይወታቸው ተጨባጭ ውጤት በሚያመጣ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የማህበራዊ ልማት አካል ተደርጎም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
የአርሶአደር ዳመነ ወላንቾ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችልና ለሌሎችም ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፤ በአሩሲ ሞጊሲ ቀበሌ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በአርሶ አደሮች ይዞታ የታየው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች በሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍተው እንዲሰሩም እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
አርሶአደር ዳመነ ወላንቾ በይዞታቸው ከመኖሪያ ቤታቸው እንስሳትን በመለየት የግልና የአካባቢው ንጽሕናን በመጠበቅ፣ የዶር እርባታ፣ የወተት ላሞችን በማርባት፣ የእንሰትና ሌሎች አትክልቶችን በማልማት ሞዴል መሆናቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ባለሙያዎችን ምክር በመቀበል ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ መሆን መቻላቸውን አርሶአደር ዳመነ ተናግረዋል።
አርሶ አደር ዳመነ በቀበሌው ሌሎች አርሶአደሮች የርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉም እያስተማሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጎቦሻ መና ቀበሌም የአርሶአደር ባሳ ባንቴ የገጠር ኮሪደር የልማት ስራዎች የጉብኝቱ አካል ናቸው።
እየታየ የመጣው የገጠር ኮሪደር ልማት ተሞክሮ በሁሉም ዘንድ ሊሰፋ እንደሚገባም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሰለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ተጠናቀቀ
የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ
የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ የሆነው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በራስ አቅም የመቻላችን ምልክት ነው ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሮች ተናገሩ