በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች በጤና የልማት ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች በጤና የልማት ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች በጤና የልማት ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ፡፡

በዋካ ከተማ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመመረቁ ደስተኛ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከ1 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው ሆስፒታል ከ1 መቶ ሺህ በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በምረቃው ዕለት እንደተናገሩት፤ መንግሥት እንደ አገር የጠራ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በማኅበራዊ የልማት ዘርፍ ዓይነተኛ ሚና በሚጫወቱ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ በመሆኑ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

በተለይም በክልሉ በጤና ተቋማት የበቁ ባለሙያዎች እንዲኖሩና የመሠረተ ልማት ክፍተት ለማሟላት፣ የቁሳቁስ ችግሮችንና የመድኃኒት እጥረቶችን ለመፍታት በተከናወነ ሥራ ውጤት እየተመዘገ ይገኛል ተብሏል።

ታክመው መዳን የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ በማኅበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድኅን ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት የጤና ተቋማት ተደራሽነት ተረጋግጦ ነዋሪዎች በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በክልሉ 4 ሆስፒታሎች መመረቃቸውንም ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው፤ ይህ ሆስፒታል በቀድሞ ክልል ተጀምሮ ግን ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት አጠቃላይ ከ1 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ተገንብቶ ሊጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ከሆስፒታሉ ግንባታ ጋር ተያይዞ ለመብራትና ለውኃ ዝርጋታ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማደረጉንም ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ለአገልግሎት ሲበቃ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል እንዲሁም የእናቶችና ሕጻናትን ሞት በማስቀረት ረገድ ድርሻው ላቅ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

ሆስፒታሉን በሰው ኃይልና በሕክምና ግብአትና ቁሳቁስ ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ ርብርብ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በክልሉ አሁን ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ የሚገኙ ሆስፒታሎችን ጨምሮ የጤና ሽፋኑ 33.4 ከመቶ የነበረውን ወደ 36.1 ከመቶ ከፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

አሁን በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን በቁጥር ወደ 13 ያሳደገ እንደሆነም ተብራርቷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደተናገሩት፤ የሕዝቡን የረጅም ዓመታት ጥያቄን በተደራጀ ሁኔታ እየተመለሰ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉም ሆነ በዞኑ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት የመብቃት የሚያስችል ተግባር ላይ ትኩረት ተደርጓልም ብለዋል።

የጤና አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኙ ለማድረግ በተከናወነው ተግባር የጤና ሽፋንን ከፍ እንዲል ያስችላልም ተብሏል።

የዋካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢዩኤል ታደሰ እንደገለፁት፤ የዋካ ሆስፒታል ለከተማውና ለአጎራባች ወረዳዎች የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በትኩረት ይሠራል።

ለሆስፒታሉ ሥራ ማስጀመሪያ ይሆን ዘንድ የታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ በሆነው ወጪ የተገዛውን የሕክምና ቁሳቁስና ከ2 መቶ ሺህ ብር ለመድኃኒት ግዥ ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን የዞኑ አስተዳዳሪ 1 ሚሊዮን ብር ስጦታ ሰጥቷል።

ሕንጻውን በመገንባት እንዲጠናቀቅ ያደረገው የጌታቸው አባተ ሕንጻ ጠቅላላ ተቋራጭ 3 መቶ ሺህ ብር ስጦታ ለሆስፒታሉ መስጠት መቻሉም ተገልጿል።

የሆስፒታሉ መመረቅ ከዚህ ቀደም ሩቅ ቦታ በመሄድ የሚደርስባቸውን እንግልት የሚያስቀር በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ ዋና አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች፣ የዳውሮ ዞን አመራሮችና የማረቃ እና የማሪ መንሣ ወረዳዎች እንዲሁም የታርጫና ገሣ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የተገኙ ከፍተኛ አመራሮች የአረንጓዴ ልማት አሻራ ለማሣካት የተያያዘውን ዕቅድ ለማሣካት እንዲቻል በሆስፒታሉ በተዘጋጀው ቦታ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን