የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የመስተዳድሩን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ተቀብሎ አጸደቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምክር ቤቱ በ6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች እቅድ ሪፖርት ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ የማስተካከያ ሃሳብና አስተያየት አክሎበት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የምክር ቤቱ አባላት በወይቦ መስኖ ልማት ግንባታ መጓተት፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመንገድና ትራንስፖርት መሰረተ ልማት፣ በንግድና ገበያ ልማት የኑሮ ውድነትና የሸማቾች መብት ጥበቃ፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር፣ ከስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አቅርበው በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል።
ከንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክልሊ አዳኝ፥ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በማከናወን ሽፋን በማሳደግና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተመላክቷል።
ከዚህ ጋር አያይዘውም ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ እንዲረዳ የማቺንግ ፈንድ ዞኖች ካልመደቡ በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ሊገጥመን ስለሚችል ዞኖች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማቺንግ ፈንድ እንዲመድቡ ጠይቀዋል፡፡
ከጤና አኳያ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የቢሮው ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፥ የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር ሴክተሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ከግንባታ ማስፋፋት ባሻገር ለህክምና ግብዓትና መድሃኒት አቅርቦት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል።
በክልሉ 30 የሚሆኑ የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድሃኒት ማቅረባቸውን ተናግረው፥ ይህንኑ ተግባር የበለጠ ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸው፥ የወባ ጫና ያለባቸው አከባቢዎችን በመለየት የኬሚካል ርጭት ከማድረግ ባሻገር 100 ሺህ የሚደርሱ አጎበር ማሰራጨት መቻሉን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ በበኩላቸው በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማጎልበት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ የአፈር አሲዲቲንና የዘር አቅርቦት ችግር በዘላቂት ለመፍታት እይተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋርና የራስ አቅምን ለማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተገንዝቦ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፥ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሆነ ከሜካናይዜሽን አንፃር በክልሉ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጥሮ ምክንያት የደረሱ አደጋዎችን ለመከላከል ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ችግሩን በራስ አቅም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ከሌማት ትሩፋት አንፃር በክልሉ ለውጦች ቢኖሩም ወጥነት ያለው ደረጃ አለመድረሱና በተለይ ከወረዳ ወረዳ፣ ከቀበሌ ቀበሌ እንዲሁም ከዞን ዞን የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ልዩነቶችን ወጥ ለማድረግ አፅንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም ጠቅሰዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት በክልሉ 91 የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም ለህብረተሰቡ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን የጠቆሙት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን፥ በመደበኛ ገበያዎችም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና በህገወጥ የነዳጅ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ አካላትን በህግ የማስጠየቅ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ፍትሃዊ የልማትና መለካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጾ የምክር ቤት አባላትም ለዚሁ ተግባር ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው የተመላከተ ሲሆን፥ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ሪፖርት በአንድ ድምፀ ተአቅቦ እና በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
በተጠናቀቀው በጀት አመት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ልዩ አርማ ሆኖ በታሪክ አሻራ ይመዘገባል ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገለፁ
ወጣቶች የነገ ለምለምና ውብ ሀገርን ለመረከብ ከአካባቢ ጀምሮ በበጎ ተግባራት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተጠቆመ