የመንገድን ደህንነት ህጎችን በማክበር የትራፊክ አደጋ እንዲቀነስ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
በከተማው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በግንዛቤ ሥራ ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ገለጿል፡፡
ወጣት ኢያሱ ብርሃኑና አቶ ጴጥሮስ መኮንን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በመኪና መንገድ በሚጠቀሙበት ጊዜ የመንገድ ደህንነት ህጎችን አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀው በዚህም የትራፊክ አደጋ እንዲቀነስ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትራፊክ ፖሊሶች ለከተማው ማህበረሰብ በየጊዜው ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ ሁሉም አካላት የሰው ህይወት በትራፊክ አደጋ እንዳይቀጠፍና የንብረት ውድመት እንዳይደርስ ለትራፊክ ህግ ተገዢ በመሆን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት የትራፊክ ፖሊሶች ቡድን መሪ ዋና ሳጅን መልካሙ ተስፋዬ፥ የትራፊክ ፖሊሶች፣ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የህዝብ አገልጋዮች መሆናቸውን በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፀው ኅብረተሰቡን ማገልገል ለአደጋው ቅነሳ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመገንዘብ በትኩረት መሠራቱን አስረድተዋል።
በአሽከርካሪዎች ስነ ምግባርና በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ዙሪያ በተደራጀ መንገድ ለማህበረሰቡና ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የመስጠት ስራዎች የተከናወነ መሆኑን ቡድን መሪው ተናግረዋል።
የትራፊክ አደጋ የማይመለከተው የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አደጋውን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ዋና ሳጅን መልካሙ አሳስበዋል።
በጽ/ቤቱ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር መብራቴ ምንዳዬ በገበያ፣ በሐይማኖት ተቋማት፣ በት/ቤቶች፣ በመናኸሪያና በመሳሰሉት ሰው በሚበዛባቸው አከባቢዎች ለእግረኞችና አሽከርካሪዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተሠራ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ መመዝቡን አስረድተዋል።
በ2016 ዓ.ም 5 የሰው ሞት፣2 ከባድ ጉዳትና 2 ቀላል ጉዳት መከሰቱን የገለፁት ኃላፊው በ2017 ዓ.ም 2 የሰው ሞት፣1 ከባድ ጉዳትና 0 ቀላል ጉዳት መውረዱን ገልፀው፣ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ጥሩ ውጤት እንዲመዘብ ኃላፊነት በተላበሰ ስብዕናን ለመሥራት ታስቦ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ገዳይነቱና ጎጂነቱ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ትርፍ ሆነው ባለመሳፈርና ለትራፊክ ፖሊሶች ትክለኛው መረጃ በመስጠት ተሳፋሪዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ምክትል ኢንስፔክተር መብራቴ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በኮሌጁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በተለያዩ የሙያ መስኮች በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን በስልጤ ዞን የሳንኩራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስርያ ቤት የ2017 በጀት አመት አቅድ አፈፃፀም በሙሉ ድምፅ ፀደቀ
የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በማረጋገጥ በስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጥ የሚችል ተወዳዳሪ እና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ትምህርት ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለፀ