የክረምት  በጎ  ፍቃድ  አገልግሎት  ወጣቶች ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን የሚያሳዩበት ተግባር መሆኑ ተገለፀ

የክረምት  በጎ  ፍቃድ  አገልግሎት  ወጣቶች ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን የሚያሳዩበት ተግባር መሆኑ ተገለፀ

“በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ “ ከፍታ በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ. ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ተካሂዳል።

‎የአሪ ዞን ፕላን መምሪያ ሃላፊ አቶ ደመላሽ አቦነ የክረምት  በጎ  ፍቃድ  አገልግሎት  ወጣቶች ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን የሚያሳዩበት ተግባር መሆኑን ገልፀው በዞኑ  ካሉ  ወረዳዎች በደቡብ አሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ስለሚገኝ ለሌሎች ሞዴል የሆነ ስራን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎የደቡብ አሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ሀይሌ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ወጣቶች በመልካም ፍቃዳቸው በርካታ የማህበረሰቡን እንባ የሚያብሱ ከ22 ሚልየን ብር በላይ ከመንግስትና ከህዝብ ሊወጣ የሚችል በጀት ማዳን የቻሉ ስራዎችን በመስራታቸው አመስግነው  በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትም  በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ  በ15 ችግር ፈች በሆኑ የትኩረት መስኮች ላይ በቅንጅት ስራዎችን እንደሚሰሩ  ገልፀዋል።

‎የወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮናስ አልቅሽ ከዚህ ቀደም በነበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የታዩ ድክመቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና በዘንድሮው የበጎፍቃድ አገልግሎት በተቀመጡ የትኩረት መስኮች ላይ በወረዳው ባሉ 34 ቀበሌያት ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በማሳተፍ  ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ተግባሩ በልዩ ትኩረት ይመራል ብለዋል።

‎‎

‎በጎነት ለራስ ነው ያሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች እንዳሉት በጎ ተግባር ማድረግ ወጣቱ ለራሱ የአዕምሮ እርካታ የሚያገኝበትና በፈጣሪም ዘንድ  የሚባረክበት ተግባር በመሆኑ  ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በይበልጥ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

‎በዕለቱም የአንድ አቅመ ደካማ ቤት በአዲስ ለመገንባት ግብአቶችን በማቅረብ ማስጀመር ተችላል።

በወረዳው ለረጅም አመታት በመምህርነትና በአመራርነት ስያገለግሉ የቆዩት አቶ ቦጋለ መተክያ በመንግስትና በወጣቶች በተደረገላቸው የቤት ማስጀመርያ ደስተኛ በመሆናቸው  አመስግነው እንደሳቸው ያሉ አቅመ ደካሞችን ቤት ለቤት በመሄድ እንዲጠይቁ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

‎ 

‎በዘንድሮ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች እንዲሁም የመንግስትና የእምነት ተቋማትን በማሳተፍ  የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ ተብሏል፡፡

‎  ዘጋቢ: በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን