የሴቶች ልማት ህብረት መጠናከር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ተግባራትን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ የጋሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ አስታወቀ

የሴቶች ልማት ህብረት መጠናከር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ተግባራትን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ የጋሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ አስታወቀ

‎በልማት ህብረቱ በመሳተፋቸው ይበልጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሴቶች ተናግረዋል።

‎በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ተገኝተን ያነጋገርናቸው አንድነት 7 የሴቶች ልማት ህብረት አባል የሆኑት ወ/ሮ አደሶ ጋሶ እና ወ/ሮ አበበች ጀርጋ በሴቶች ልማት ህብረት በጤና፣ በትምህር፣ በግብርናው፣ በቁጠባና ብድር የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጡ ይገኛሉ።

‎ በዚህም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀን ከህብረቱ ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።

‎የልማት ህብረቱ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አበበች ጋቢኖ፤ ልማት ህብረቷ ቁጠባን ባህል በማድረግ የሴቶችን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ በየቀበሌው ለችግር የተጋለጡ ሴቶችን በመደገፍ እና በግብርና ዘርፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረትና ተፈጥሮአዊ ይዘቱን የጠበቀ ሰብል በማምረት ተጠቃሚ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

‎ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የልማት ህብረቷ ሰብሳቢ ወ/ሮ አስናቀች አበራ፤ የሴቶች ልማት ህብረት በየቀበሌው በተሰጠ ውስን ቦታ ሙዝ በማምረት፣ በሳምንት አንድ ቀን የጥጥ ፈተላ ቀን በመሰየም ጋቢ እያመረቱ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን አውስተዋል።

‎በተጨማሪም የማገዶ ቆጣቢ ምድጃን በስፋት በማምረት ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

‎የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ መርጊያ ማጃ፤ በወረዳው 780 ልማት ህብረት አደረጃጀት 2 ሺ 29 አባላት እንደሚገኙ አብራርተዋል።

‎ሴቶች በየአደረጃጀታቸው ሰለ ጤና፣ ትምርት ኢኮኖሚን እንዴት ማሻሻል እንዳለባቸው የሚወያዩበትና ችግሮችን በጋራ የሚፈቱበት በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

‎የጋሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሂሩት ማሞ፤ የሴቶች ልማት ህብረት መጠናከር የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ተግባራትን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ አስታውቀዋል።

‎የልማት ህብረቱ ለችግር የተጋለጡ እናትን በመርዳት እና መልሶ በማቋቋም በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው ለሌሎች አካባቢ ሴቶች አርአያ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።

‎በዞኑ 9 ሺ 368 የልማት ህብረት አደረጃጀት እንዳለ ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን