በክልሉ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት በራስ አቅም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

በክልሉ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት በራስ አቅም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ: ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት በራስ አቅም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በክልሉ የአደጋ ተጋላጭነት ፕሮፋይል ጥናት ካልተጠናባቸው ወረዳዎች መካከል በ1 ወረዳ (ሰላማጎ) አደጋ ተጋላጭነት ጥናት እና 6 ወረዳዎች (ዳሰነች፣ ኛንጋቶም፣ ሐመር፣ በናጸማይ፣ ማሌ፣ እና ኮላንጎ ዙሪያ) ከአሁን በፊት የተጠና የአደጋ ተጋላጭነት ጥናት ክለሳ ለማድረግ በታቀደው መሰረት እየተሰራ መሆኑን ገለጹ፡፡

በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት እና ለሥጋት ለተጋለጡ የቤተሰብ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በማስተባበር 627 የቤተሰብ ኃላፊዎችን ተደራሽ ለማድረግ 494፣ በሌሎች ቀበሌያት ደግሞ በህብረተሰቡ ተሳትፎ 60 በድምሩ 554 መኖሪያ ቤቶች ተጠናቅቀው ለተጎጂ ወገኖች የተላለፈ መሆኑን ጠቁመው፥ ቀሪዎቹ እየተገነቡ ሲሆን፥ ተጨማሪ 300 ቤቶችን ከአጋር አካላት ጋር ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

አዲስ በተሰሩ መንደሮች ውስጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማደራጀት 110 ሽንት ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ፣ የእንስሳት ጤና ኬላ እና ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የሚሆን አንድ ብሎክ ትምህርት ቤት ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የአንድ ሁለተኛ ትውልድ የጤና ኬላና የአንድ ትምህርት ቤት ጥገና እንዲሁም የአንድ ትምህርት ቤት ግንባታ መደረጉን ገልጸዋል።

በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ 420 ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለዶሮ ልማት ብር 384,750 እና ለአነስተኛ አመንዛኪ እንስሳት ብር 6,000,000 በማመቻቸት 40 የወተት ላሞች፣ 212.5 ኩ/ል ዳፕ፣ 212.5 ኩ/ል ዩሪያ እና 67.5 ኩ/ል ምርጥ ዘር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተው፥ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ብር 42,444,500 የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በመርመርቴ ማዕከል የሰዉ እና የእንስሳት ጤና ኬላ እንዲሁም የመጠጥ ውኃ ግንባታ ሲጠናቀቅ በቻይና መንገድ ማዕከል ባለ አራት ክፍል ትምህርት ቤት የንጽህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ቢጠናቀቅም መንደሩ በውሃ ሊጥለቀለቅ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በአርኮል፣ በከለም፣ በአርሳሟይና ሰለኝ ማዕከላት አንዳንድ የትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም በአሪኬል አንድ ጤና ኬላ እየተሰራ ሲሆን፥ በዳሰነች ወረዳ የኦሞና የቱርካና ወንዝ ወደኋላ መፍሰስን ለመከላከል ጊዜያዊ መከላከያ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ርዐሰ መስተዳድሩ፥ ዘላቂ ማስተንፈሻ ለማካሄድ ጨረታው ተጠናቅቆ ወደስራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የኦሞራቴ ከተማንና ሌሎች አስጊ ቀበሌያትን ለመታደግ ከስጋት ነጻ ቦታ መረጣና ህብረተሰቡን የማወያየት ስራ እየተሰራ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል፡፡

በወላይታ ዞን በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በአበላ አባያ፣ በሆቢቻና ኪንዶ ኮይሻ ለማስፈር 800 ቤቶችን ለመገንባት እየተሰራ ነው ያሉት ርዐሰ መስተዳድሩ፥ ለዚህም በዞንና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ብር 48 ሚሊየን መሰብሰቡን ጠቁመው፥ የቤት ግንባታ ሂደት ተጀምሮ 102 ቤቶች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በጋሞ ዞን አስጊ ቀበሌና አካባቢዎችን በመለየት ከስጋት ነጻ በሆኑ ቦታዎች 510 ተፈናቃዮችን ለማስፈር 14 ሚሊዮን ብር በመመደብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቁመው፥ በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ ለተፈናቀሉ 193 የቤተሰብ ኃላፊዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በኮንሶ ዞን መልሶ ለማቋቋም ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር 137 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በሰገን ዙሪያ፣ ኮልሜ እና ካራት ዙሪያ ወረዳዎች 1,530 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በኮሬ ዞን በሰርመሌ ወረዳ አንድ ብሎክ ባለ 4 ክፍል ትምህርት ቤት በግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እየተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ የቤት ግንባታ ስራዎችን በፋብሪካ ዕቃዎች ለመደገፍ በክልሉ መንግሥት 50,000 የቤት ኪዳን ቆርቆሮና 3,720 ፓኬት ምስማር ተገዝቶ በወላይታ መጋዘን እየተገነባ ይገኛል፡፡

ለመጠባበቂያ ክምችት የሚሆን ምግብ ከማዘጋጀት አንጻር በ2016 መኸር ወቅት በ3,006 ሄ/ር 150,300 ኩ/ል ለማምረት በክልል ማዕከል በግብርና ስራ በተሰማሩት ባለሀብቶች ማሳ 1,600 ሄ/ር አርሶ 64,000 ኩ/ል ለማምረት ታቅዶ 1,366 ሄ/ር ተዘርቶ 20,435 ኩ/ል ተሰብስቦ ወደ መጋዘን የገባ ሲሆን በዞንና በወረዳ 1,800 ሄ/ር ለመዝራትና 90,000 ኩ/ል ለማምረት ታቅዶ 569 ሄ/ር ተዘርቶ 2,233 ኩ/ል የተለያዩ ዓይነት እህል ተሰብስቧል፡፡

በክልል፣ በዞኖች እና በወረዳ የተሰበሰበው አጠቃላይ ምርት 22,668 ኩ/ል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የአስቸኳይ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ በክልሉ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በክልሉ አቅም ለመደገፍ እንዲቻል በየደረጃው የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ ፈንድ ማቋቋሚያና ማስፈጸሚያ ደንብ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በጸደቀው መሠረት በየደረጃው ሀብት መሰብሰብ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ከዞኖች ብር 313,016,386 (63%) ተሰብስቧል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ