በክልሉ ያለው የምርትና ምርታማነት እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለጸ

በክልሉ ያለው የምርትና ምርታማነት እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ: ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ያለው የምርትና ምርታማነት እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ለደቡብ ትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን አስፈፃሚ ተቋማት ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ በክልሉ ያለው የምርትና ምርታማነት እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ የመጣበት መሆኑን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በዋና ዋና ሰብሎች የክልሉ አማካይ የምርታማነት ዕድገት 2016/17 ምርት ዘመን ከ2015/16 ጋር ሲነጻጸር የበቆሎ ምርታማነት በ2015/16 ከነበረበት 25 ነጥብ 52 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 32 ነጥብ 7 ኩ/ል በሄ/ር ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የጤፍ ምርታማነት በ2015/16 ከነበረበት በ12.47 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 13.47 ኩ/ል በሄ/ር ማድረስ መቻሉን ጠቁመው፥ የቦሎቄ ምርታማነት ከነበረበት 11.79 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 16.39 ኩ/ል በሄ/ር ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

የስንዴ ምርታማነት ከነበረበት 28.61 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 29.4 ኩ/ል በሄ/ር አድጓል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የማሽላ ምርታማነትን ከነበረበት 17.78 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 22.14 ኩ/ል ማሳደግ መቻሉን ገልፀው፥ በሄ/ርና የሰሊጥ ምርታማነትን ከነበረበት 5.44 ኩ/ል በሄ/ር ወደ 6.46 ኩ/ል በሄ/ር ለማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደዚሁም አማካይ የቡና ምርታማነት በ2015/16 7.43 ኩ/ል ሄ/ር የነበረ ሲሆን በ2016/17 ወደ 8.26 (11.17%) እና የቅመማ ቅመም አማካይ ምርታማነት 58.3 ኩ/ል ሄ/ር የነበረውን ወደ 62.6 ኩ/ል ሄ/ር ለማድረስ መቻሉን ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት አመላክተዋል።

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ሥራ በ2016/17 ምርት ዘመን ምርት ከሚሰጠው 164,385 ሄ/ር ማሳ 135,939 ቶን ምርት ለማምረት ታቅዶ 114,509 (84%) ቶን ማምረት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የቡና ምርታማነትን በአማካኝ በሄ/ር 9.2 ኩ/ል ለማድረስ ታቅዶ 8.26 ኩ/ል/ሄ/ር ለማግኘት የተቻለ ሲሆን በሞዴል አርሶ አደሮች በአማካይ 18 ኩ/ል በሄ/ር ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ