በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

ምክር ቤቱ 3ኛ ዙር 11ኛ የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነው በየም ዞን ሳጃ ከተማ እያካሄደ ያለው።

በጉባኤው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፤ ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት አራት የትኩረት መስኮች ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በበጀት አመቱ በተለይ በክልሉ የተስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ስለመደረጉ አንስተዋል።

በህገ መንግስት እና ፌደራሊዝም ዙሪያ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን የተናገሩት ዋና አፈ ጉባኤው በዚህም ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በሌላ በኩል በተጠናቀቀው የ2017 በጀት አመት በክልሉ የተከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው፤ በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ተወካይ ምክር ቤቶች በባለቤትነት ስሜት በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነና ለዚህሞ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቀጣይ 20ኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በክልሉ አስተናባሪነት የሚከበር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሃላፊነት ስሜት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ አቡቶ አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው ጉባኤ የብሔረሰቦች ምክር ቤት 3ኛ ዙር 11ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤን መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን የ2017 እቅድ አፈጻጸም፣ የ2018 የምክር ቤቱን እቅድና የ2018 በጀት አመት የበጀት ቀመርን በተመለከተ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ ከጉባኤው መጀመር አስቀድሞ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሳጃ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል።

ዘጋቢ: ወንድወሰን ሽመልስ