ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ከዞን እስከ ወረዳ የህዝቡን አስተያየት መሠረት በማድረግ በተሰራው ስራ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተፈቱበት በጀት አመት ነበር ሲል የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ
ፍርድ ቤቱ የ2017 በጀት አመት አፈፃፀምና የ2018 በጀት አመት እቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚዛን አማን ከተማ የምክክር መድርክ አካሂዷል።
የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በስሩ ስድስት የወረዳ ፍርድ ቤትና አራት የከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ፍርድ ቤቶች ይገኛሉ።
እነዚህን በስሩ አድርጎ እየሠራ የሚገኘው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተጠናቀቀው በጀት አመት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ነው የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ቢንያም ባቡ የገለፁት።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ህብረተሰቡ አስተያየት እንዲሰጥ ተደርጎ እሱን መሠረት በማድረግ በተከናወነው ስራ ይታዩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተፈቱበት እና የአቅም ግንባታ ስራዎች የተሰሩበት አመት መሆኑን ገልፀዋል።
የማህበራዊ ፍርድ ቤት እና ባህላዊ ዳኝነቶች አዋጅ ወጥቶ በ152 ቀበሌዎች የማህበራዊ ፍርድ ቤቶችን አስልጥኖ ወደ ሰራ ማስገባት እንደተቻለ አመልክተዋል።
በዚህም በመደበኛ ፍርድ ቤት ከታዩት መዝገቦች ባሻገር በ25 መዝገቦች ላይ ውሳኔ የተሰጠ በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀረቡ 7 ሺ 22 መዝገቦች ውስጥ 6 ሺ 512 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መሠጠቱ ተመላክቷል።
ቀሪዎቹ 510 መዝገቦች ለ2018 በጀት አመት መዛወራቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።
ፍትህን በሁለት ወራት የመወሰን አቅምን 92 በመቶ ለማድርስ ታቅዶ ወደ ስራ ቢገባም በአመት ውስጥ ውሳኔ ከተሰጠባቸው 6 ሺ 512 መዝገቦች ውስጥ 5 ሺ 167 መዝገቦችን በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ በመስጠት የእቅዱን 80 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ተመላክቷል።
የማጥራት አቅምን በተመለከተ አዲስ ከቀረቡ 6 ሺ 464 መዝገቦች ወስጥ 6 ሺ 512 መዝገቦች ላይ ውሳኔ በመስጠት የማጥራት አቅምን ከእቅድ አንፃር መቶ በመቶ መፈፀሙ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በፍርድ ቤቱ ስራ ላይ የተገኙት የየፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ ዳኞችን እና ባለድርሻ አካላት በፍርድ ቤቱ የተሻለ አፈፃፀም እንዳለ አስተያየት ሰጥተዋል።
ከአቅም ግንባታ እና ከበጀት አንፃር ዳኞች ላነሷቸው ጥያቄዎች በፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት በአቶ ቢንያም ባቡና በምክትል ፕሬዝዳንቱ በአቶ ሻንበል ቦሽ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በስሩ ካሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት አመት ግብ ስምምነት ከማድረጋቸው በተጨማሪ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላሣዩ ፍርድ ቤቶች እና ሰራተኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ አሳሳኸኝ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው
የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳደር ከዞኑ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቡታጅራ ከተማ ወይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል
ወጣቱ ከሀገር ተረካቢነት ባለፈ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሩ ለውጥ መስራት እንዳለበት ተገለጸ