ወጣቱ ከሀገር ተረካቢነት ባለፈ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሩ ለውጥ መስራት እንዳለበት ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወጣቱ ከሀገር ተረካቢነት ባለፈ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሩ ለውጥ መስራት እንዳለበት የደቡብ ኦሞ ዞን አስታወቀ።
በ2017 ዓመተ ምህረት በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚከናወኑ ተግባራት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና ህዝብ ወጭ ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምርያ አስታወቀ ።
በጎነትን ከፍ በማድረግ የህዝባችንን ነባር የአብሮነትና አንድነት ዕሴቶችን አጠናክረን እናስቀጥላለን በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት መዝጊያ እና የ2017 ዓ/ም የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ዞናዊ ንቅናቄ ተካሂዳል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ወጣቱ ከሀገር ተረካቢነት ባለፈ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገሩ ለውጥ መስራት እንዳለበት ተናግረው በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን በይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ተግባሩ በልዩ ትኩረት ይመራል ብለዋል።
አክለውም የዳሰነች ማህበረሰብ በኦሞ ወንዝና በቱርኳና ሀይቅ ሙላት ምክንያት እየደረሰበት ካለው ችግር ለመታደግ ወጣቶችም ሆኑ መዋቅሮች የበጎነት ባህልን በማጎልበት ማህበረሰቡን መርዳት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምርያ ኃላፊ አቶ ጥጋቡ ጎረጊ 93 ሺ 800 ወጣቶችን በማሳተፍ ከ124 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለዩ 13 የትኩረት መስኮች በተጨማሪ የፋይዳ መታወቂያ ኢትዮ ኮደርስና የስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ወጭን ለማዳን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች እንዲሁም የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የእምነት ተቋማትና የበጎ አድራጎት ማህበራትን በማሳተፍ በተለዩ የትኩረት መስኮች የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ጥጋቡ ጎረጊ ገልፀዋል።
በዞኑ የማሌ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ ደጀኔ አገኘሁ እና የዲመካ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ሃላፊ አቶ ተሾመ ግርማ በጋራ በዘንድሮ የክረምት ወራት በአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ግንባታና እድሳት፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በግብርና ዘርፍ፣ በትምህርት አገልግሎት፣ በጤና መስክ፣ በገቢ አሰባሰብና ንግድ ፍቃድ እድሳት፣ የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ህፃናት መብታቸዉና ደህንነታቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወላይታ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ገለጸ
የሕብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የአገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ