ህፃናት መብታቸዉና ደህንነታቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወላይታ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ገለጸ

ህፃናት መብታቸዉና ደህንነታቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወላይታ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ገለጸ

ይህ የተገለፀው የወላይታ ዞን የህጻናት ፓርላማ 6ኛ ዙር 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ነው።

በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አበዛሽ ዳንኤል፤ ህፃናት መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚያድጉ ከሆነ የነገ ሀገር አለኝታ ይሆናሉ ብለዋል።

ስለሆነም ህፃናት ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ህፃናት መብታቸዉና ደህንነታቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ህፃናት በእነሱ ላይ የሚደርስባቸውን ማንኛውንም ጥቃቶች መከላከል እንዲችሉ በየደረጃው የሚገኘውን የህጻናት ፓርላማ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክረምት ወቅት የሚከናወኑ የበጎ አገልግሎት ሥራዎች ላይ ህፃናት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ምቹ ሁነታ መፈጠር እንደአለበት ጠቁመዋል።

በተለይም በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል አኳያ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለው ለዚህም የህብረተሰቡ ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የዞኑ ህጻናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባኤ ህፃን ቢኒያም ትዕግሥቱ በሰጠው አስተያየት፤ ከወላጆች እቅፍ በተለያዩ ምክንያቶች ወደጎዳና ህይወት የሚወጡ ህፃናት ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች ዘግናኝ ናቸው በማለት ድርጊቱን ለመከላከል የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ብሏል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ህፃን ሶልያና አማኑኤል እና ህፃን ናርዶስ መሸሻ፤ ህፃናት ለወላጆች መታዘዝ አለባቸው በማለት ህፃናት ላይ የሚደረሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በተለይም ወላጆች ከፍተኛ ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን