የሕብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የሕብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የኣሪ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የ2017 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ተግባርን በጂንካ ከተማ በይፋ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያው መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፋት የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ ወጣቱ በበጎ አገልግሎት በመሳተፍ የማህበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንዲቀርፉና መልካምነትን በሕይወታቸው እንዲለማመዱ ዞኑ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን በማሳተፍ የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ የግብርና ሥራዎችን ማሳለጥ፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን በማከናወን አካባቢያቸውን ማልማት እንዳለባቸው የገለፁት የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ ናቸው።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሉቃስ ቡሪ በበኩላቸው፤ የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ተግባራት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ንቅናቄ መጀመሩን ገልፀው ወጣቱ በጎነትና አብሮነትን ባህል በማድረግ ለሀገር እድገት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

በክረምት በጎ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተሳተፉ ወጣቶች ለሀገራቸው ዕድገትና ከፍታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረው፤ ሌሎችም እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ መርሃ-ግብርም ተከናውኗል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን