በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የአገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የአገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

ይህ የተገለጸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም በወልቂጤ ከተማ በገመገመበት ወቅት ነው።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት ወልደሰንበት እንዳሉት፤ በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የአገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ እርካታ ማሳደግ ይገባል።

ይህንን ተግባር እውን ለማድረግ ተቋሙ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ የሰው ኃይል አቅም ለማጎልበት እያከናወነ የሚገኘው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ተቋሙ ለውጤታማ ባለሙያዎች እና ተቋማት እውቅናና ሽልማት በመስጠት በባለሙያውና በተቋማት መካከል ጤናማ የስራ ውድድር እንዲኖር ከማድረግ ጎን ለጎን ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ለመዘርጋት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል ወይዘሮ መሰረት።

የኢንስፔክሽን ግኝቶችን ለማረም የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉት የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ ከስራ ሰአት አጠቃቀም ጋር ያሉ ክፍተቶችኝ በመቅረፍ እንዲሁም የአድርባይነት አመለካከት እና አስተሳሰብ በማስወገድ ጠንካራ ሠራተኛና አሰራር ዘርግቶ ለህዝብ ተጠቃሚነት መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በየተቋሙ የሚመደበው በጀት በአግባቡ ለታለመለት አላማ ከማዋል እንዲሁም እየተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥራትና በተያያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ምላሽና ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ፤ ከዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንደግብዓት ተወስደው ለቀጣይ የስራ አካል እንደሚያደርጓቸው ተናግረዋል፡፡

አክለውም በክልል ማዕከል ያለው የሰው ኃይል እጥረት ከበጀት ጋር የተያያዘ ውስንነት በመሆኑ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አመላክተዋል ሀላፊው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል የድጋፍና ክትትል እንዲሁም ግንዛቤ የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ኃላፊው፤ በቅጥርና ዝውውር ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ግልጸኝነትና ወጥነት ያለው ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን