ሀዋሳ፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገሪቱን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማደረግ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡
“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለሀገራዊ ሉዓላዊነትና ለተሟላ ክብር” በሚል መሪ ቃል የቀበሌ፣ የወረዳ እና የከተማ አመራሮች የምክክር መድረክ በይርጋጨፌ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላፉት የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን፥ በሀገራችን ስር ሰዶ የቆየውን የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብ በማስወገድ ህዝቡን ወደ ላቀ ምርታማነት ደረጃ ማሸጋገርና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የአደጋ ስጋት አይበገሬነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስዳዳሪ አቶ ዳዊት በበኩላቸው፥ በወረዳው የሚገኙ ጸጋና ሀብቶችን አሟጣ በመጠቀም ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተለያዩ ስራዎችን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፥ እየተሰራ ያለው ሥራ ከሰብዓዊ ድጋፍ ተላቆ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለ ጥረት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ይርጋጨፌ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ ያለው አከባቢ ከመሆኑም ባለፈ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመለየትና በመምራት ሀገራችንም ሆነ ክልሉን ከተረጂነት እሳቤ ማውጣት እንደሚገባም አስተዳዳሪዎቹ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ሰነድ ያቀረቡት የከተማውና ወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ አቶ መብራቱ ኦብሴና ዘርሁን አሰፋ በራስ ዓቅም በማምረት ከውጪ የሚገቡ ምርት መጠን በመቀነስ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማደረግ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የሚከሰቱ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋምና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመድረስ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተጋገዝበትን ስርዓት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ጅግሶ፥ በ2016/17 ምርት ዘመን በስንዴ ምርት የተሻለ አፈፃፀም ካስመዘገቡ ቀበሌያት መካከል ቱቲት፣ ኡዴሳና ጭርቁ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው አሁን ላይ በአንድ ሄክታር 28 ኩንታል ማግኘት መቻሉን ገልፀው፥ ይህንን ተሞክሮ ወደ ሌላ ቀበሌ ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡
አሁን ላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የኑሮ ውድነት ጫና እያሳደረ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ ችግሮቹ የሚፈታበትን መፍትሄ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የክልሉን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በ2018 በጀት አመት በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ምርጫ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሐምሌ 10/2017 ጀምሮ እንደሚያካሂድ ተገለፀ
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ #ደሬቴድ፣ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም