የክልሉን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በ2018 በጀት አመት በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

የክልሉን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በ2018 በጀት አመት በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ሀዋሳ: ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በ2018 በጀት አመት በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ።

በትናንትናው ዕለት የጀመረው የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ምርጫ ዘመን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ሁሉም ዘርፍ የተከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ በዝርዝር የመከረው ምክር ቤቱ፥ ግልፅነትና ማብራሪያ በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየቶችን በማንሳት በጥልቀት ተወያይቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ፥ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉን መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ የስራ እቅድ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን ህዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል የክልሉ መንግስት የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ሲሰራበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

የቤተሰብ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችሉና የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ በተለይም ግብርናውን በማዘመን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ፥ በሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን ለመጨመር እንደሚሰራ በቀረበው እቅድ ተመላክቷል።

ከ258 ሺህ በላይ የእንሰሳት ዝርያዎችን ማሻሻል፣ የንብ ቀፎዎችን ወደ 158 ሺህ ማሳደግ እና በዘርፉ ተያያዥ ስራዎችን በስፋት ለመስራት መታቀዱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የግብር ከፋዮችን ቁጥር ከፍ በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መተቀዱን አስረድተዋል።

አልሚ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ በመሳብ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት፣ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሻሻልና፥ ከ29 ሺህ በላይ ወጣቶችን በቴክኒክና ሙያ ለማሰልጠን መታቀዱን ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት እቅድ አመላክተዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሽፋንን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በክልሉ 70 አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን የመገንባት እና ሌሎች ነባር ፕሮጀክቶችን ለማደስ መታቀዱን ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ፣ ዕድሚያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ማስገባት፣ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ማድረስ፣ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ50 ፐርሰንት በላይ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በ2018 በጀት አመት እንደሚከናወን ርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው እቅድ ላይ አመላክተዋል።

በቀጣይ በጀት አመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣ የህዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው እቅድ መሠረት እንደሚከናወኑ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራ ገልፀው፥ ከዚህ ጎን ለጎን የተጠያቂነት ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ዕቅድ አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ