የቦንጋ፣ ኦዳ ጭዳ የአስፓልት መንገድ በግንዛቤ ክፍተት ሳቢያ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑ ተጠቆመ

የቦንጋ፣ ኦዳ ጭዳ የአስፓልት መንገድ በግንዛቤ ክፍተት ሳቢያ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቦንጋ፣ ኦዳ ጭዳ የአስፓልት መንገድ በግንዛቤ ክፍተት ሳቢያ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ የኦዳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኦዳ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት በበኩሉ የአስፓልት መንገዱ የዲዛይን ችግር ያለበት ቢሆንም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋለዉ የግንዛቤ ክፍተት ሊስተካከል የሚገባዉ ነዉ ብሏል።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ይህ መንገድ በአካባቢዉ በመንገድ እጦት ሳብያ ይከሰቱ የነበሩ ችግሮች በአንጻራዊነት ለመቅረፍ ያስቻለ መሆኑ ይነገርለታል።

ይሁንና አካባቢዉ አመቱን ሙሉ ዝናብ የማይቋረጥበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የናዳ እና መሰል ተፈጥሮአዊ ችግሮች መንገዱን ለብልሽት ከመዳረጋቸው ባሻገር እንቅስቃሴዎችንም ሲገታ ማየት የተለመደ ነዉ።

በከተሞች አካባቢ ይህ የአስፓልት መንገድ የዲዛይን ችግር ያለበት በመሆኑና በአንዳንደ የአካባቢው ነዋሪዎች በግንዛቤ ጉድለት ለብልሽት እየተዳረገ ይገኛል ተብሏል።

በኦዳ ከተማ ካነጋገርናቸዉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቆጭቶ ወልደሰንበትና አቶ አትርሴ ታደሰ በሰጡት አስተያየት በከተማዉ የእግረኛ መንገድ ላይ የንግድ ስራዎችን መከወን፣ የግንባታ እቃዎችን ማዉረድ፣ ፈረሶችን ማሰር እና መሰል ችግሮች ለአስፓልት መንገዱ መበላሸት ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

ያለዉን ሃብት በአግባቡ እየተጠቀሙ የአስፓልቱ መሰረታዊ ችግር እንዲቀረፍ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ነዋሪዎቹ የወረዳዉ አስተዳደሩ እና ማዘጋጃ ቤቱ ህዝቡን የማስተባበር ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኦዳ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መከተ ቆጭቶ መንገዱ በመሰረታዊነት የዲዛይን ችግር ያለበት መሆኑን የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ማህበረሰቡ ላይ በአንዳንድ ነዋሪዎች ዘንድ በሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶች ሳቢያ ለጉዳት ተዳርጓል ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የሰዉ ሃይል እጥረት እንቅፋት እንደሆነ የገለጹት ሃላፊዉ በዘንድሮዉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራና በጎርፍ የተጎዳዉን የመንገዱን አካል የማሰተካከል ስራ ይሰራል ብለዋል።

የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የአስፓልቱን ዕድሜ የማራዘም ጉዳይ ለነገ የማይባል ነዉ ያሉት የወረዳዉ አስተዳዳሪ አቶ አበራ አደቆ በከተማዉ የዲች ቦይ ላይ የንግድ ስራ የሚከዉኑና ፈረሶችን የሚያስሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ትዕግቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን