መንግስት አንድ የተጠናከረ የጸጥታ ኃይል ለማደራጀት በሚያደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግስት አንድ የተጠናከረ የጸጥታ ኃይል ለማደራጀት በሚያደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ከማደራጀት አኳያ የተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከ6ቱም ዞኖች ከተውጣጡ የፖሊስ አመራር አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል፡፡
መንግስት የተጠናከረ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ኃይልን ለማደራጀት ባደረገው እንቅስቃሴ የክልሎችን ልዩ ኃይል መልሶ በማደራጀት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመልሶ ማደራጀቱ ዋና አላማ ሀገራዊ ራዕይና ተልዕኮውን መወጣት የሚችልና ለዜጎች ክብርና ለህገ መንግስቱ መከበር ኃላፊነቱን በጽናት የሚወጣ የጸጥታ ኃይል ማደራጀት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው ገለፃ ያደረጉትና የምክክር መድኩን የመሩት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ናቸው፡፡
የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ከማደራጀት አኳያ በአንዳንድ አካባቢዎች በተዛባ መንገድ የሚነሱ ነገሮችን ተከትሎ ማንም ሚዛናዊነት የጎደለ እሳቤ ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል አቶ አንድነት፡፡
የጸጥታ ሥራ እንደተለመደው በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰራ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ተልዕኮአቸውን በተቀናጀና በተሰናሰነ ሁኔታ እንዲቀጥሉ አቶ አንድነት አሳስበዋል፡፡
የልዩ ኃይል መልሶ ከማደራጀት አኳያ በሀገር ደረጃ የተደረገው ጥናት ጸድቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይ ምክትል ኮሚሽነር ከበደ ደበበ ናቸው፡፡
የክልሉ ልዩ ኃይል ከዚህ ቀደም በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ በቁርጠኝነት ተልዕኮውን ሲወጣ የቆየ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ አሁንም በተመደቡበት ክፍል የመደበኛ ፖሊስ ባህሪን በመላበስ በብቃት እንዲወጡ መክረዋል፡፡
ከኮሚሽነሮች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት አባሉ በአዲሱ አደረጃጀት ደስተኛ መሆኑን ተናግረው በዚሁ መሠረት በተመደቡበት ክፍል ተልዕኮአቸውን መወጣት እንዲችሉ ቀጣይ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ከምክክር መድረኩ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ: መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የመመለስና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)