ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የህብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ጸረ-ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የህብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጸረ-ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ለሀገር ዕድገትና ለሰላም መስፈን እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል ሙስናና ብልሹ አሰራር መስፋፋት ሲሆን ይህንንም ለመከላከል የሚያስችል የጸረ-ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህ መሠረትም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የጸረ-ሙስና ትግሉን ማስቀጠል እንዲቻል ኮሚቴ አቋቁሞ መስራት ከጀመረ ወዲህ 160 የሚሆኑ ጥቆማዎችን ተቀብሎ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ጸረ-ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት አበበ ተናግረዋል፡፡
የቀረቡትን ጥቆማዎች ደረጃ በደረጃ በመጣራት ሂደት ላይ እንደሚገኙ የኮሚቴው ሰብሳቢ አስረድተዋል፡፡
በማጣራት ሂደት ውስጥም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ያለባቸው አካላት ተለይተው እንዲቀርቡ አቅጣጫ የተሰጠባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አቶ አስራት አመላክተዋል፡፡
በዚህ መሠረት በ6 መዝገቦች ላይ ማጣሪያ ተደርጎ ክስ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት አቶ አስራት 20 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 14 ሰዎች በፍርድ ቤት እየተፈለጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በአብዛኛው በክልል ደረጃ እየቀረቡ ያሉት የሙስና ጥቆማዎች ከፋይናንስ፣ ከተማና ገጠር መሬት ወረራ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች እንደሆኑም አቶ አስራት አክለዋል፡፡
ከ6ቱ መዝገቦችና ከሌሎች የፋይናንስ አሰራር ግድፈት ጋር በተገናኘ ከ35 ሚሊዮን በላይ ብር በቀረበው ጥቆማ መሠረት እየተጣራ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ ገልፀዋል፡፡
በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መሠረት ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወደ መንግስት ካዝና ማስመለስ መቻሉን የተናገሩት አቶ አስራት የፀረ-ሙስና ትግሉን በመደገፍ ረገድ የካፋና የቤንቺ ሸኮ ዞኖች በአርአያነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ የዳውሮና የሸካ ዞኖች ቀዝቀዝ ያሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምንም ጥቆማ ያላደረጉ ዞኖች መኖራቸውን ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላትና የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አስራት አሳስበዋል፡፡
የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው የጸረ-ሙስና ትግሉን ለማስቀጠል የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሥነ-ምግባር ኦፊሰሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ