በአከባቢ የመጣውን ሰላም በማስጠበቅና በማስቀጠል በኩል ህዝቡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

በአከባቢ የመጣውን ሰላም በማስጠበቅና በማስቀጠል በኩል ህዝቡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአከባቢ የመጣውን ሰላም በማስጠበቅ እና በማስቀጠል በኩል ህዝቡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ፡፡

ክልሉ ሰላምን ለማስፈን በሰራው ስራ እና ባስመዘገው ውጤት ሊመሰገን እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈትቤት የተቋማት ክትትል እና የካቢኔ ጉዳይ ሚኒስተር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ ተናገሩ።

ሀገራዊ የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት እና ተባባሪ ተቋማት በደቡብ ምእራብ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ የማስጀመሪያ ፕሮግራም በተከናወነበት ወቅት የደቡብ ምእራብ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደተናገሩት ክልሉ እንደ ክልል ከተደራጀ ወዲህ የክልሉን ሰላም ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ አከባቢዎች ይከሰቱ የነበሩት የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት ተችለዋል ብለዋል።

ለዚሁ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በእነዚህ በጉረፈርዳ ወረዳ አሮጌ ብርሀን ይከሰት የነበረው የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ተፈቶ አሁን አርሶ አደሩ በእርሻ ስራ በመሉ አቅሙ መሰማራቱ አንዱ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል። ይህን የመጣውን የሰላም ውጤቶች ህብረተሰቡ ሊጠብቅ ሊያስቀጥልም እንደሚገባ ነው ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ የተናገሩት።

ወጣቶችም የታላላቆቻቸውን እና የቤተሰባቸውን ምክር በመቀበል ለአከባቢ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ርእሰ መስተዳደሩ።

በጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት የተቋማት ክትትል እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስተር ዴኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች የነበሩትን የጸጥታ ችግሮች የክልሉ መንግስት ለመፍታት በሄደባቸው መንገዶች ውጤት መገኘቱን ገልጸው በዚሁ የክልሉ መንግስት የአመራር አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ይህንን መልካም ተግባርም ህዝቡ ሊደግፍም ይገባልም ብለዋል።

የጉረፈርዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታጋይ ኤልያስ በበኩላቸው በወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የጸጥታ ችግር ተቀርፎ ዛሬ ሰላሙን ህዝቡ አረጋግጦ ወደልማት መግባቱን ጠቁመው የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በጉረፈርዳ ወረዳ የአሮጌ ብረሀን ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው የመጣውን ሰላም በማስጠበቅ እና ልማቱን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን