ሐምሌ 24 ለሚካሄደው በአንድ ጀንበር 21 ሚሊዬን ችግኝ ለመትከል ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሐምሌ 24 ለሚካሄደው በአንድ ጀንበር 21 ሚሊዬን ችግኝ ተከላ ለማካሔድ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ማስረሻ በላቸው ተናገሩ።
እስካሁን 185 ሚሊዬን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውም ተጠቁሟል።
እንደ ሀገር ከ2011 ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር ከተጀመረ በኋላ በባለፉት ስድስት አመታት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ የችግኝ አይነቶች መተከላቸው ተመላክቷል።
የዚሁ አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ አንድ አካል የሆነው እና የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በደቡብ ምእራብ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉረፈርዳ ወረዳ በአሮጌ ብረሃን ቀበሌ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም እና የችግኝ ተካላ መረሐ ግብር የደቡብ ምእራብ ክልል ርእሰ መስተዳደሩ ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልል እና የዞን የወረዳ አመራሮች በተገኙበት አካሂደዋል።
በዚሁ መረሐ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የደቡብ ምእራብ ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደተናገሩት፥ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በክልሉ 399 ሚሊዬን በላይ ችግኞች በበልግ ወቅት እና በመኸር ወር እንደሚተከሉ ተናግረዋል።
ከሚተከሉ ችግኞች ውስጥ ስልሳ ከመቶዎቹ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች ይሆናሉ ብለዋል።
የመጀመሪያ ዙር የበልግ ተከላ ፕሮግራም እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ መጠናቀቁን ጠቁመው ዋነኛ የተከላ ፕሮግራም መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
በበልግ ውስጥ 185 ሚሊዬን ችግኝ መተከሉን ያስታወሱት አቶ ማስረሻ ቀጣይ እስከ መስከረም አስራ አምስት 195 ሚሊዬን ችግኞች እንደሚተከል ገልጸው፥ አጠቃላይ በክልሉ ከሚተከሉ 399 ሚሊዬን ችግኝ ውስጥ 79 ሚሊዬን ችግኞች የቡና ችግኞች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አሁን የመኸር ተከላ ላይ መሆናቸውን እና የዚሁ ተከላ አካል የሆነው ሐምሌ 24 ቀን የሚከናወነው በአንድ ጀንበር 21 ሚሊዬን ለመትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን የደን እና ፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ሪከርድ ለመያዝ ጥረት እንደሚያደርጉ እና ለዚሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ጉረፈርዳ ወረዳ አሮጌ ብረሃን በተካሄደ የችግኝ ተከላ መረሐ ግብር ከፌደራል ከክልል እንዲሁም ከዞን የተገኙ የአመራር አካላትም በችግኝ ተከላው አሻራቸውንም አሳርፈዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በአከባቢ የመጣውን ሰላም በማስጠበቅና በማስቀጠል በኩል ህዝቡ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ
የገጠር ኮሪደር ልማት ከሌማት ቱርፋት ጋር በማስተሳሰር የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ተገለጸ
በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሠቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት አስመረቀ