በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሠቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት አስመረቀ

በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሠቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት አስመረቀ

ሀዋሳ፡ ሐዋሳ 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሠቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሀዲያ ዞን በሆመቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት አስመረቀ።

የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቱ አስፈላጊ መድሀኒቶችን በማሟላት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት አላማ አንዱ የሆነውን የማህበረሰብ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በአከባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎችን ለተገልጋዩ ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ተገቢ ህክምና ማግኘት እንዲችሉ የሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል።

በሀድያ ዞን ከሚገነቡ አራት ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች አንዱ የሆነው የሆመቾ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት ከ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አስፈላጊ መድሀኒቶችን በማሟላት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ዶ/ር ዳዊት ገልፀዋል።

የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ይድነቃቸው ደዳቸው ይህ ስራ የማህበረሰቡን የመድሀኒት እጦት በእጅጉ የሚፈታ እንደሆነ በመጠቆም ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የምናደርገውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ነዉ ብለዋል።

የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ተወካይ አቶ ሚሻሞ ወርቅነህ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በማስፋት በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የመድሀኒት እጥረት ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል ።

የሆመቾ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ታምሬ በበኩላቸው የሆመቾ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ መድረሱን ተናግረዋል ።

ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም ለ 2 አመታት አገልግሎት እስከማቋረጥ ደርሶ እንደነበር ያነሱት ስራ አስኪያጁ በከተማ አስተዳደሩ እና በባለድርሻ አካላት ርብርብ መልሶ ወደስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ዩኒቨርስቲው እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በሆስፒታሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል ።

ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎችም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት መገንባቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ።

በምረቃ መረሐ ግብሩም ላይ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እና የስራ ሀላፊዎች፣ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ፣ የባህል ሽማግሌዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን