በበጋው ወቅት የተሰሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር አቅመደካማ ወገኖችን የመደገፍ ስራ መስራት እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

በበጋው ወቅት የተሰሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር አቅመደካማ ወገኖችን የመደገፍ ስራ መስራት እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መዝጊያና የክረምት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ እንደገለፁት፤ በበጎ አድራጎት ስራ በሃገር አቀፍ በክልልና በልዩ ወረዳ ደረጃ በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት በመከናወናቸው ተጨባጭ ውጤቶች ማምጣት ተችሏል።

በተለይም ለአቅመ ደካማ ወገኖች ቤት መጠገንና አዳዲስ ቤቶች መገንባትን ጨምሮ ሌልችም የበጎ አድራጎት ስራዎች ልዩ ወረዳው ላይ በትኩረት መሰራቱን ያነሱት አቶ ሞሳ፤ በዚህም ከመንግስት ካዝና ወጪ ሊደረግ የነበረን በሚልዮኖች የሚገመት ሃብት ለሌላ ልማት እንዲውል ማድረግ አስችሏል ብለዋል።

በመሆኑም በበጋው ወቅት የተሰሩ ውጤታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በክረምቱም ይበልጥ በማጠናከር ድጋፉ የሚሹ አቅመደካማ ወገኖችን በቅርበት የመለየትና የመደገፍ ስራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚገባም ነው የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ የተናገሩት።

የልዩ ወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል በበኩላቸው፤ በጎነት ለራስ መሆኑን የተረዳው የልዩ ወረዳው ህዝብና ወጣት በዚህ ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎትና ተነሳሽነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ ወገኖች ቤት ግንባታ፣ ትምህርትና ጤናን ጨምሮ በተለያዩ 12 ዘርፎች ላይ ከማህበራዊ ዋስትና፣ ከሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤቶችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በዚህም ከ30 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሆኑና በገንዘብ ሲተመን ከ15 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በበጋው ወራት የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን መነሻ አድርጎ በመውሰድ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም 49 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ከ25 ሚልዮን ብር በላይ ከመንግስት ካዝና ሊወጣ የሚችል ገንዘብ ለሌላ ልማት እንዲውል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል አቶ ጁሃር።

የመረሃግብሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ባለፉት የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፋቸውን በመግለፅ በሁሉም ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ነበሩ ብለዋል።

በቀጣይም በሚሰሩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በተሻለ መልኩ ለመሳተፍና ማህበረሰባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን