የብልጽግና መንግስት ከፌደራል ደረጃ ወደታች ወርዶ የሚያከናውናቸው ሰው ተኮር በጎ ተግባራት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው – የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የብልጽግና መንግስት ከፌደራል ደረጃ ወደታች ወርዶ የሚያከናውናቸው ሰው ተኮር በጎ ተግባራት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ገለፀ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በአራዳ ቀበሌ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በፌዴራል መንገድ ደህንነት እና መንገድ ፈንድ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን እና በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በ8 ሚሊየን 5 መቶ ሺ ብር የተገነቡ 3 ዘመናዊ የአቅመ ደካማ ቤቶች የምረቃ ፕሮግራም ተካሂዷል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ፤ በሀገራችን በ2014 ዓ.ም በመንግስት የተጀመረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መተግበር ከጀመረ ወዲህ በክረምትና በጋ ወራት በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራት የዕቅድ አካል ተደርገው እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በዕለቱ ተገንብተው ለምርቃት የበቁ የአቅመ ደካሞች እና አረጋውዊያን ቤቶች እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ የለውጡ መንግስት ያስጀመራቸው የማህበረሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል መሆናቸውንም አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር፣ በመድን ፈንድና በኢትዮጵያ አቪየሺን ባለስልጣን በተገኘው ከ8 ሚሊየን በሚበልጥ ብር 3 መኖሪያ ቤቶች የተገነቡ ሲሆን በ5 መቶ ሺ ብር ደግሞ ሙሉ የቤት ዕቃዎች ተሟልተዋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የቤቶቹ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን የጠቆሙት ከንቲባ ዳዊት፤ ይህን በጎ ተግባር የፈጸሙ የፌዴራል ተቋማትን አመስግነዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዋና አማካሪና የአስተዳደሩ ተወካይ አቶ ታምራት አኑሎ በበኩላቸው፤ በመንግስ የተጀመረው የአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃን የማሻሻል ተግባራት የበርካቶችን ህይወት እየቀየረ ይገኛል ብለዋል።
አሁን የተጀመረውን አነስተኛ የማህበረሰብ በጎ አገልግሎት በማስፋት በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ለማዳረስ የሃይማኖት ተቋማት፣ ባለሀብቶችና የመንግስት አካላት በቅንጅት የመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫላ ፋይሳ፤ ወደታች ወርዶ ሁሉም አካባቢዎች በብልጽግና መንግስት የተጀመረውን ሰው ተኮር ተግባራትን በማህበረሰብ ውስጥ መከወን በሀገር አንድነት፣ ሠላምና ልማት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጫላ፤ መንግስት ወደታች ወርዶ መስራትን ለአብነት ለማሳየት መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ትምህርት ቤቶችን እና ለአቅመ ደካሞች የመኖሪ ቤቶችን መገንባቱን ጠቁመው፤ ለተማሪዎች ለመማር ማስተማር የሚውሉ ቁሳቁሶችን የመደገፍ ስራ ማከናወኑን አቶ ጫላ አውስተዋል።
በ2016 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በ1.2 ሚሊየን ብር ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የፍጆታ ዕቃና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ዘንድሮ ደግሞ በ8 ሚሊየን ብር ለ3 አቅመ ደካሞችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤት የገነባ ሲሆን ለዚህም 10 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን አቶ ጫላ አብራርተዋል።
ተቋሙ ከበጎ ተግባራቱ ጎን ለጎን በ2018 ዓ.ም 7.5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ማቀዱንም ጠቁመዋል።
ቤት የተገነባላቸው አረጋውያንና አቅመ ደካሞች በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ እንደሚኖሩና አሁን ግን በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያስመዘገበች ላለችው የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲል የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ
በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን አጽንቶ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ ገለፁ
በኮንታ ዞን ጳጉሜን 1 – የጽናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል