ከ14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሠማራታቸው ተገለጸ

ከ14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሠማራታቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017 በጀት ዓመት ከ14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሠማራታቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለአልሚ ባለሐብቶች መሰጠቱም ተጠቁሟል።

በክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የፕሮሞሽን ፈቃድና ዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይደነቅ ወልደሰንበት እንደገለፁት ለተለያዩ ኢንቨስትመንት አገልግሎቶች መዋል የሚችል ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በክልሉ በገጠርና በከተሞች ላይ ተለይቶ ይገኛል።

ክልሉ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑም በየዓመቱ የአልሚው ባለሀብት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ በ2014 ዓ.ም ሲመሰረት 655 የነበረው የአልሚ ባለሀብቶች ቁጥርም 364 ጨምሮ አሁን ወደ 1,019 ማደጉን አቶ ይደነቅ አስረድተዋል።

በ2017 በጀት ዓመትም 14 ቢሊዮን 407 ሚሊዮን 794 ሺህ 121 ብር በጀት ያስመዘገቡ 114 ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ መሰማራታቸውን አብራርተዋል።

18 ሺህ 244 ሄክታር መሬትም ለአልሚ ባለሀብቶቹ አልፎ መሰጠቱን አቶ ይደነቅ ጠቁመዋል።

ወደ ስራ ከገቡት አልሚ ባለሀብቶች መካከልም በግብርና ዘርፍ የተሰማሩት ከ51 በመቶ በመውሰድ አብላጫውን ድርሻ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

አሁን በክልሉ ከሚገኙ 1,019 ፕሮጀክቶች መካከልም 19ኙ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ፕሮጀክት ነው ብለዋል አቶ ይደነቅ።

ወደ ስራ የገቡት ፕሮጀክቶች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ከ95 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

መሠረተ ልማትና ሎጀስቲክ ዕጥረት በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ወደ ስራ የገቡት ባለሀብቶችም ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፈ 168.6 ኪሎሜትር የፕሮጀክት መዳረሻ መንገዶችን መገንባታቸውን አቶ ይደነቅ አብራርተዋል።

ባለሀብቱ በገባው ውል መሠረት ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ይደነቅ አንስተው አስካሁን መሬት ወስደው ወደ ማልማት ያልገቡ ከ48 ፕሮጀክቶች ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተቀንሶ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

በ2017 በጀት ዓመትም 36 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ይደነቅ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን