ሁለንተናዊ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ምክር ቤቶች መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

ሁለንተናዊ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ምክር ቤቶች መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶች ዘርፍ ጋር በጋራ ክልል አቀፍ የወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።

በምስረታ ጉባኤው ላይ የተገኙት በኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ አማካሪ ወ/ሮ የሺወርቅ አያኔ፣ የተደራጀው ምክር ቤት ጠንካራ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በአገር ደረጃ ከ41 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይገኛሉ ተብሏል። በመሆኑም ለዚህ የሚመጥን አደረጃጀት መፍጠር የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመድረኩ ተነስቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ እንደተናገሩት፤ የምስረታው ዓላማ በሁሉም ዘርፎች የወጣቶችን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለመንግሥት ውሳኔ በማቅረብ ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው።

በመድረኩ ዞኖችንና ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞችን የሚወክሉ 15 ወጣቶች እንዲሁም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች ተመርጠው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

በምስረታው ላይ የተገኙ ወጣቶች ሂደቱ አሳታፊና አካታች እንደነበር ተናግረዋል።

በምስረታው ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የክልል፣ የ12 ዞኖችና የ3 ሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች የወጣት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: አማሮ አርሳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን