የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች እና ተቋማት የምስጋና እና የዕውቅና መርሀ ግብር በወላይታ ሶዶ እየተከናወነ ይገኛል።
የደም ለጋሾች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ “የህይወትና የብርሀን ስጦታ ያበርክቱ፤ ደምና ብሌን ይለግሱ” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ በመከበር ላይ ይገኛል።
በዓሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፍተኛ ደም ለጋሾች፣ የደም ልገሳ ማህበራትና ተቋማት በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ በክልሉ 8 ነጥብ 4 ሚሊየን ህዝብ እንደሚኖር አውስተው ደም መለገስ ለተጎዱ ወገኖች ህይወትን መስጠት፣ የአይን ብሌን መለገስ ደግሞ የህይወት ብርሀን መስጠት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ደም ለጋሾች ጀግኖቻችንና አምባሳደሮቻችን ናቸው ያሉት አቶ ተፈሪ፤ የደምና የአይን ብሌን ልገሳን ለማበረታታትና ለማሳደግ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወነ ይገኛል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የብሄራዊ ደም ባንክ ደምና ህብረ ህዋስ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ጤናዬ ደስታ፤ ደም መለገስ የመልካምነት ማሳያ በመሆኑ ደም በመለገስ የሰውን ህይወት መታደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ከደም የሚገኘውን መድሀኒት ሀገር ውስጥ በማምረት በጤናና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና መታደግ እንደሚያሻ አብራርተዋል።
በሀገራችን 55 የደም ባንኮች እንደሚገኙና ከእነዚህም መካከል 5ቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚገኙ ያብራሩት ዳይሬክተሯ፤ እነዚህን ባንኮች ከማጠናከር ባሻገር አስፈላጊውን ደም ማሰባሰብ እንዲቻል ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ከደን ምንጣሮ የፀዳ ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እተየሰራ ነው
የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኙ
ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ