የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለታለመላቸው ዓላማ መዋል እንዲችሉና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለታለመላቸው ዓላማ መዋል እንዲችሉና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ በ130 ሚሊዮን ብር የተገነባውን ቃንቅቾ ገበታ የዉሃ ፕሮጀክት ርክክብ ተደርጓል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ንፁህ የመጠጥ ዉሃ በማግኘታቸው መደሰታቸውንና ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል::
በዞኑ ዱና ወረዳ ዋገበታና ቃንቅቾ ቀበሌያት ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ንፁህ የመጠጥ ውሃ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ባለመሆኑ ለተለያዩ እንግልቶች ሲዳረጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም በአካባቢያቸው የተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች ንፁህ የመጠጥ ውሃ መግኘት መጀመራቸውን የተናገሩ ሲሆን ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው በባለቤትነት በመጠበቅ ጉድለቶችን በጋራ ለማሟላት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
በሀዲያ ዞን የዱና ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ገ/ወልድ ላላፉት ዓመታት በወረዳው የሚስተዋለውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር አውስተው ለብዙሃኑ ተደራሽ እንዲሆን የተበላሹ መስመሮችን የመጠገን ማህበረሰቡ በባለቤትነት እንዲከታተል የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።
የሀዲያ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መመሪያ ኃላፊ አቶ መለስ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የቃንቅቾ የውሃ ፕሮጀክት በዞኑ ከተገነቡ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑንና ከ41 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ታልመው የተገነቡ 40 የውሃ ቧንቧዎች ያሉት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ቀጣይነት ባለው መልኩ የማህበረሰቡን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲቀርፍ ጉድለቶችን በመለየት ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች የመጨረሻ ርክብክብ በተደረገበት ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጡሞሮ፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለታለመላቸው ዓላማ መዋል እንዲችሉና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ጥገና በማከናወን ቀሪ ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከ1 መቶ 30 ሚለዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገነባ የውሃ ፕሮጀክቶች በተገቢው ተደራሽ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ላይ ቢሮው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ሙላቱ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ የተሻለ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደር ገለፀ
2ኛ ዙር የማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የ2017 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰጠ ነው
የሚገነቡ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ