ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንድሁም ለህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንድሁም ለህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ለህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን በዳውሮ ዞን የሎማ ቦሳ ወረዳ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

‎የጽ/ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ እታገኝ ኢሳያስ እንደገለፁት በሰቆጣ ቃልኪዳን የሚከናወኑ ተግባራት በወረዳው መቀንጨርን ዜሮ ለማድረስ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተግባራትን ሽፋን ከፍ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

‎ድጋፍ በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌያት መካከል ከፉላሣ ቦርዜ፣ ላላ አምቤ፣ ዚማ ዋሩማ፣ ጭጮ ሃዮ እና ከቱለማ ጣማ ቀበሌያት ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንድሁም ለህፃናት ድጋፍ መደረጉን ወ/ሮ እታገኝ ተናግረዋ።

‎በሰቆጣ ቃል ኪዳን እስካሁን በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ እታገኝ፥ እናቶች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር የአኗኗር ዘይቤ መቀየር የሚያስችሉ እንዲሁም ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ሥራዎች መሰራቱን ገልጸዋል።

‎የወረዳው የህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ክብረዓለም በቀለ በበኩላቸው፥ የጨቅላ ህፃናት መቀንጨር ለመከላከልና በዚህም ሳቢያ ሊመጣ የሚችለውን ሞት ለመቀነስ የወተት ላም፣ በግና ፍየል እንዲሁም ዶሮ ግዢ በመፈጸም ስርጭት ማድረጉን አብራርተዋል።

‎በተጠናቀቀው በ2017 በጀት ዓመት በሰቆጣ ቃል ኪዳን ከ52 በላይ ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንና ከ50 በላይ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።

‎በፕሮግራሙ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በተቻለ መልኩ ለማግኘት ጅምር የሚሆኑና የተሻለ ስራዎችም ተሰርተዋል ነው ያሉት።

‎ድጋፍ ካገኙ ነፍሰጡርና ከሚያጠቡ እናቶች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት “አሁን ያገኘሁት ድጋፍ የቆየውን የምግብ እጥረት ችግሩን የሚቀርፍ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን