የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የ2017 በጀት ዓመት የግብር አሰባሰብ በወልቂጤ ከተማ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በግብር አሰባሰብ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህግ ማስከበር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ውድነህ፥ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመሰጠት ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ መክፈል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እንደ ክልል በበጀት አመቱ 16 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።

በተለይ አሁን ላይ በወልቂጤ ከተማ እየተከናወነ ያለው በርካታ ልማታዊ ስራዎች ከግብር ከፋዮች በተሰበሰበው ገንዘብ እንደሆነ አስታውሰው፥ ነጋዴዎች በቀጣይም የተጀመሩ ልማታዊ ስራዎች ለማፋጠን የግብር አከፋፈልን በተያዘው ጊዜ ከፍሎ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ፥ መንግስት ለዜጎች የሚያቀርባቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሸፈነው ከግብርና ከታክስ ከሚያገኘው ገቢ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በተቀናጀ መልኩ ለማስከፈል ተግባሩ መጀመሩን የገለፁት አቶ ሚነወር፥ ጊዜው የግብር ወቅት በመሆኑ ግብር እና ታክስ በወቅቱ በመክፈል ግብር ከፋዮች የዜግነት ግዴታቸውን በተገቢው መንገድ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ የገቢ ተቋማትም የግብር አከፋፈል ስርዓቱን ለግብር ከፋዮች ምቹ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው፥ ግብር የሁሉም ነገር መሠረት እንደሆነ ገልጸው በተለይም የልማት፣ የመልካም አሰተዳደር፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሁሉም ቁልፍ ጉዳዮች በመሆኑ ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የተዘጋጁለትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ሳይዘናጋ ከዛሬ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተዘጋጁ የመክፈያ ማዕከላት በመሄድ እንዲከፍል ጥሪ አስተላልፈዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰፋ ዘይኑ በከተማው በበጀት ዓመቱ ገቢ በተገቢው መሰብሰብ እንዲቻል ለግብር ከፋዮች በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም የወልቂጤ ከተማ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የሚነሱ የልማትና የመልካም አሰተዳደር ችግሮች ምላሸ ለመሰጠት በበጀት ዓመቱ 1ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተቀዶ ከ774 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። የተሰበሰበው ገቢ ከአምና ወቅት ጋር ሲነጸጸር የ68 በመቶ ብልጫ መኖሩን አቶ ሰፈ አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ የነበሩ ጥንካሬዎችን ይበልጥ በማጠናከር ድክመቶችን በማረም በ2018 በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

በወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር በጊዜያዊነት ግብር መክፈያ በተዘጋጀው ስፍራ ላይ ዓመታዊ ግብራቸውን ለመክፈል የመጡ ግብር ከፋዮች በሰጡት አስተያየትም በከተማው ከሚያገኙት አመታዊ ገቢ ላይ ለመንግሥት የሚገባውን ታክስ በወቅቱና በታማኝነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ኂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን