ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ዓመታዊ የደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር አከፋፈል በንቅናቄ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂንር ዳግማዊ አየለ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ከመንታ መንገድ ወጥታ የገቢ አማራጮችን በማሳደግና ከዕርዳታ በመላቀቅ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሏን ገልጸዋል።
የበለፀገ አካባቢ እንዲኖር ለማስቻል በገቢ ስወራ ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምትክል ኃላፊና የግብር ከፋዮች ግንዛቤ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግርማ ምትኩ፤ በክልሉ የገቢ ዕድገት ላይ የታማኝ ግብር ከፋዮች አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
አካባቢው ከግብርና ምርቶች አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ይህንን አቅም ወደ ገቢ በመቀየር የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መኮንን፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዞኑ ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በዞኑ በተደራጁ 12 ዋና ማዕከላትና በ37 ንዑሳን ማዕከላት 10 ሺህ 019 ደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን መክፈል መጀመራቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 3 ቪህ 325 ግብር ከፋዮች በቴሌብር ግብራቸውን የሚከፍሉ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
የሳውላ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ኩማ፤ ግብር ከእኛ ተሰብስቦ ለኛ ልማት የሚውል የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ነው ብለዋል።
በከተማው 2 ሺ 656 የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰው በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
የከተማ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል የታቀደውን ዕቅድ እናሳካለን ብለዋል፡፡
የሳውላ ከተማ ከንቲባ ንጉሴ መኮንን (ዶ/ር) ግብር በወቅቱ መክፈል የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን ገልፀው፤ በቴክኖሎጂ በተደገፈ የአከፋፈል ስርዓት ከታቀደው ጊዜ በፊት ግብራቸውን በመክፈል ወደ መደበኛ ስራ መመለስ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለተለያዩ አገልግሎቶች ደረሰኝ ጠይቆ የመውሰድ ልምዱን ሊያዳብር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ግብር በቴሌ ብር መክፈልን ባህል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ካነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች መካከል አቶ ቦጋለ ሀላላ እና አቶ እስራኤል ሜጎ በሰጡት አስተያዬት ግብር የሚከፈለው ለአገር ልማት በመሆኑ ግብራችንን በወቅቱ በመክፈል የዜግነትት ጊዴታችንን በመወጣታችን ደስተኞች ነን ተብለዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የእምርታ ቀንን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት:-
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) መልዕክት፡-
የእመርታ ቀን