ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (ደረቴድ) በ2018 በጀት ዓመት ከ 250 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ።
በወረዳው የሚገኙ 1ሺህ 55 የደረጃ”ሐ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ዓመታዊ ግብራቸውን መክፈል ጀምረዋል ።
የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ደምሴ በወረዳው የግብር ማስከፈል ስነ-ስርአቱን በበሌሳ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በግብር የሚሰበሰበው ገቢ ለህዝብ ልማት የሚዉል በመሆኑ ሁሉም ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈል አለበት ።
በወረዳው አዳዲስ የገቢ አመራጮችን በመፍጠር ከባለፈው ዓመት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪዉ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ግብር ከፋዮች በግብር አዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል በወረዳው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ታደለ አሳስበዋል ።
የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራዉ አለቃ በበኩላቸዉ በወረዳዉ 1ሺህ 88 ግብር ከፋዩች መኖራቸውን ጠቅሰው ከነዚህም መካከል 1ሺህ 55ቱ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 239 ሚሊየን 43 ሺህ 280 ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከዕቅዱ በላይ 239 ሚሊየን 45 ሺህ 250 ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው በ2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ250 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በይፋ ወደ ተግባር መገባቱን አስታዉቀዋል።
ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ በወረዳዉ በ10 ማዕካላት ግብር የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ሽፈራዉ ሁሉም ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት እንዲከፍሉ አሳስበዋል።
በወረዳዉ በተለያዩ የግብር መክፈያ ማዕከላት ያነጋገርናቸው አንዳንድ ግብር ከፋዮች በሰጡት አስተያየት ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል መንግስት የጀመራቸውን ልማቶችን ማፋጠን መሆኑን በዉል በመረዳት ግብራቸዉን እየከፈሉ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ #ደሬቴድ፣ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም
የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ለማጠናከር የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ
የኮሪደር ልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ መምጣቱን ነዋሪዎች ተናገሩ